top of page
IMG_20201216_114208.jpg
Home: Welcome

SERVICES

Untitled

27 ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያምተወልዶ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎሥጋዉን ቆርሶ ደሙን አፍሶ መድኃኒተሥጋ መድኃኒተ ነፍስ የሰጠንአባቴ ቸሩ መድኃኔዓለምይክበር ይመስገንአሜን አሜን አሜን

Untitled

✝✝✞✞✞✝ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
❖ ታኅሣሥ ፩ (1) ❖
✞✞✞✝ እንኩዋን ለታላቁ ነቢይ "ቅዱስ ኤልያስ" :"ቅዱስ ዼጥሮስ ዘጋዛ" እና "ቅድስት ቤርሳቤህ"ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
+*" ታላቁ ቅዱስ ኤልያስ "*+
=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሊቀ ነቢያት ቅዱስ ሙሴቀጥላ ቅዱስ ኤልያስን ታከብራለች:: "ርዕሰ ነቢያት - የነቢያት ራስም" ትለዋለች:: እርሱ ሰማይን የለጐመ:እሳትን ያዘነመ: ፍጥረትንም በቃሉ ያዘዘ አባት ነውና::ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
+ቅዱሱ ትውልዱ (ነገዱ) ኢዮርብዓም ነጥሎከወሰዳቸው እሥራኤል (10ሩ ነገድ) ሲሆን አባቱ"ኢያስኑዩ" : እናቱ ደግሞ "ቶና (ቶናህ)" ይባላሉ:: በጐአምልኮ ነበራቸውና እግዚአብሔር ማሕጸነ ቶናህን ቀድሶይህንን ቅዱስ ፍሬ ፈጠረ::
+ቅዱስ ኤልያስ በተወለደ ቀን በቤታቸው ብርሃን ተሞልቶታይቷል:: ብርሃን የለበሱ 4 ሰዎች (መላእክት)መጥተውም በእሳት ሰፋድል (መጐናጸፊያ) ሲጠቀልሉትወላጆቹ በማየታቸው ደንግጠው ለነቢያትና ለካህናት ነገሯቸው::
+ካህናቱ ግን ነገሩ ቢረቅባቸው "ምን ዓይነት ፍጥረትይሆን? በእሥራኤል ይነግሥ ይሆን! ወይስ ነቢይይሆን?" ብለውም አድንቀዋል:: ቅዱስ ኤልያስ ከልጅነቱጀምሮ ኮስታራ: ቁም ነገረኛ: ንጽሕናንም የሚወድእሥራኤላዊ ነው::
+ወቅቱ (ከክርስቶስ ልደት 900 ዓመት በፊት) ሕዝቡናነገሥታቱ የከፉበት: እግዚአብሔር ተክዶ ጣዖትየሚመለክበት ነበር:: ድሮ በኢሎፍላውያን እጅ የነበሩትጣዖታት (ዳጐንና ቤል) በዚያ ዘመን ወደ እሥራኤልገብተው ነበር::
+ቅዱስ ኤልያስ ግን በዚህ ክፉ ትውልድ መካከልሆኖም ሥርዓተ ኦሪትን የጠነቀቀ: የንጽሕናና የአምልኮ ሰው ነበር::
+በዚያ ወራትም እግዚአብሔር ለነቢይነት ጠራው::እርሱም "እሺ" ብሎ ታዞ የእግዚአብሔርን የጸጋ ጥሪተቀበለ::
ቅዱሱ ብዙ ጊዜ ለጉዳይ ካልሆነ ከሰው ጋር መዋል:ማደርን አይወድምና መኖሪያውን በተራሮችና በዱርአደረገ::
+በተለይ ደብረ ቀርሜሎስ ለእርሱ ቤቱ ነበር:: በዚህሕይወቱም ከመልከ ጼዴቅ ቀጥሎ:-
1.ለድንግልና (ድንግል ነበርና)2.ለብሕትውና (ብቸኛ ነበርና)3.ለምንኩስና (ተሐራሚ ነበርና) በብሉይ ኪዳን መሠረትንየጣለ ነቢይ ይባላል::
+መቼም በብሉይ ኪዳን የቅዱስ ኤልያስን: በዘመነክርስቶስ የመጥምቁ ዮሐንስን: በዘመነ ሊቃውንት ደግሞየአፈ ወርቅ ዮሐንስን ያህል ደፋርና መገሥጽ አስተማሪአልነበረም:: በጊዜው ደግሞ አክአብና ኤልዛቤል የሚባሉክፉ ባልና ሚስት በእሥራኤል ላይ ነግሠው ሕዝቡንጣዖት አስመለኩት::
+ይባስ ብለው ደግሞ በወይኑ እርሻ አማካኝነትኢይዝራኤላዊው ናቡቴን በሃሰት ምስክር ደሙንአፈሰሱት:: ናቡቴም "የአባቶቼን ርስት አልሸጥም:አልለውጥም::" በማለቱ እንደ ሰማዕት ይቆጠራል::
+ኤልያስ ግን ይህንን ሲሰማ ወደ አክአብና ኤልዛቤልቀርቦ "የናቡቴ ደም በእናንተ ላይ አይቀርም:: የአንቺንምደም ውሻ ይልሰዋል" አላቸው:: በዚህ ምክንያትምኤልዛቤል ልትገድለው ብትፈልገውም እርሱየእግዚአብሔር ነውና አላገኘችውም::
+በዚህ ብስጭትም ይመስላል አንድ ሺህ ነቢያትንሰብስባ "ፍጇቸው" አለች:: 900ው ሲታረዱ አንድመቶውን ግን ቅዱስ አብድዩ በዋሻ ውስጥ ደብቆእየመገበ አተረፋቸው:: በእሥራኤል ውስጥ ግን ዓመጻናኃጢአት እየተስፋፋ ሔደ:: የእግዚአብሔርን ስጦታእየተመገበ ሕዝቡ ለቤል (ለበዓል) ሰገደ::
+ይህን ጊዜ ግን ቅዱስ ኤልያስ እንዲህ አለ:-"ሕያው እግዚአብሔር አምላከ ኃይል: ዘቆምኩቅድሜሁ: ከመ ኢይረድ ጠል በእላ መዋዕል ዘእንበለበቃለ አፉየ::" ብሎ ዝናም ከሰማይ እንዳይወርድከለከለ::
ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ሰማይ ዝናም ለዘር ጠልለመከር ከመስጠት ተከለከለ::
+ሕዝቡ በኃጢአቱ ምክንያት ተጐዳ:: እርሱን ቁራይመግበው: ምንጭ ፈልቆለት ይጠጣ ነበር:: ይሔውቢቀርበት ጸለየ:: እግዚአብሔርም ከፈለገ ኮራት ወደሰራፕታ እንዲወርድ አዘዘው:: በዚያም የነቢዩ ዮናስ እናትእንጐቻ ጋግራ ብታበላው ቤቷ በበረከት ተሞላ::
+ልጇ ሕጻኑ ዮናስ ቢሞትም በጸሎቱ አስነሳላት::ቀጥሎም 7 ጊዜ በትጋት ጸልዮ ለ3 ዓመታት ከ6 ወራትየዘጋውን ሰማይ ከፍቶታል:: ሕዝቡም ዕለቱኑ ከበረከቱቀምሰዋል::
+ከዚያ አስቀድሞ ግን ከኤልዛቤል 850 ነቢያተ ሐሰትናካህናተ ጣዖት ጋር ተወዳድሮ አሸንፏቸዋል:: መስዋዕትሰውተው የእርሱን ብቻ እሳት ከሰማይ ወርዳበልታለታለችና ሕዝቡ 850ውን ሐሰተኛ ነቢያት በወንዝዳር በሰይፍ መትተዋቸዋል::
+ይሕንን የሰማች ኤልዛቤልም ትገድለው ዘንድአሳደደችው:: "አቤቱ ከአባቶቼ አልበልጥምና ውሰደኝ!ብቻየን ቀርቻለሁና" ብሎ ቢጸልይ እግዚአብሔር ለጣዖትያልሰገዱ ሰባት ሺህ ሰዎችን እንዳተረፈ: እርሱንም ወደብሔረ ሕያዋን እንደሚወስደው ብሥራትን ነገረው::
+ደክሞት ተኝቶ ሳለም ቅዱስ መልአክ (ሚካኤል)ቀስቅሶ ታየው:: እንጐቻ ባገልግል: ውሃ በመንቀልአቅርቦ "ብላ! ጠጣ!" አለው:: በላ: ጠጣ: ተኛ:: እንደገና ቀስቅሶ አበላው:: በ3ኛው ግን "ብላዕ እስከ ትጸግብእስመ ርሑቅ ፍኖትከ - ጐዳናህ ሩቅ ነውናእስክትጠግብ ብላ" አለው::
+ኤልያስም ለ40 ቀናት ያለ ምግብ ተጉዟል:: ከዚያበሁዋላም ምድራዊ ሕብስትን አልተመገበም::እግዚአብሔር አክአብና ኤልዛቤልን ከተበቀላቸውበሁዋላም ቅዱስ ኤልያስ በክፋተኞች ላይ 2 ጊዜ እሳትንአዝንሟል::
+የሚያርግበት ጊዜ ሲደርስም ደቀ መዝሙሩን ኤልሳዕን"የምትሻውን ለምነኝ" ቢለው "እጥፍ መንፈስህን"አለው:: 3 ጊዜ ሊያስመልሰው ሞከረ:: ቅዱስ ኤልሳዕግን በብርታት ተከተለው:: ዮርዳኖስን ከፍለው ከተሻገሩበሁዋላ ግን ቅዱስ ኤልያስን ሠረገላ እሳት ወርዶነጠቀው:: ለኤልሳዕም እኩሉን ግምጃውን ጣለለት::
+ዛሬ ቅዱስ ኤልያስ በብሔረ ሕያዋን ያለ ሲሆን በዘመነሐሳዌ መሲሕ መጥቶ በሰማዕትነት ከቅዱስ ሔኖክ ጋር ያርፋል:: (ራዕይ)¤ለተጨማሪ ንባብ ( ከ1ነገ. 17-2ነገ. 2, እና ዕርገተ ኤልያስን ያንብቡ::)
<<ነቢዩ ኤልያስ በእውነት ታላቅ ነው!>>
+"+ ቅዱስ ዼጥሮስ ዘጋዛ +"+
=>ይህ ቅዱስ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን በታናሽ እስያአካባቢ የተወለደ ሲሆን የክቡራኑ የመሣፍንት ልጅ ነው::በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድጐ የቁስጥንጥንያ ንጉሥትንሹ ቴዎዶስዮስ ወደ ቤተ መንግስቱ ወሰደው::
+በዚያም "አገረ ገዥ ላድርግህ" ብሎ ቢጠይቀው"ትንሽ ቆየኝማ" ብሎት ጠፍቶ በርሃ ገብቶ መነኮሰ::ቅዱስ ዼጥሮስ በምንኩስና ሲጋደል: ካለበት በርሃመጥተው በግድ ወስደው: የጋዛ (አሁን የፍልስጤምናእሥራኤል ደንበር) ዻዻስ አደረጉት::
+ከደግነቱ የተነሳም በቅዳሴ ጊዜ ሥጋ ወደሙ ሲለወጥያየው ነበር:: መላእክትም ያጫውቱት ነበር:: ሕዝቡሲያጠፉ በየዋሕነት ዝም ቢላቸውም ቅዱስ መልአክ ገሥጾታል::
+የፋርስ ነገሥታት አጽመ ሰማዕታትን ሲያቃጥሉም እርሱየቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድን አጽም ይዞ ተሰዷል:: ለብዙዘመናት በቅድስና ኑሮም በዚህች ቀን ዐርፏል::
+"+ ቅድስት ቤርሳቤህ +"+
=>ይህቺ እናት አስቀድማ የኦርዮ ሚስት: ቀጥሎ ደግሞየልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ሚስትና የሰሎሞን እናትለመሆን በቅታለች:: ቁጥሯ ከደጋግ እናቶቻችን ሲሆንየድንግል ማርያም ቅድመ አያትም ናት:: አንዳንድሊቃውንት ደግሞ ስሟን "ቤትስባ (ቤተሳባ)" :ትውልዷንም ከኢትዮዽያ ያደርጉታል::
=>አምላከ ኤልያስ በምልጃው ለሃገራችንና ለሕዝቧ
ርሕራሔውን ይላክልን:: ከቅዱሳኑም በረከትን ይክፈለን::
=>ታሕሳስ 1 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=1.ቅዱስ ኤልያስ ርዕሰ ነቢያት2.ቅዱስ ዼጥሮስ ዘጋዛ3.ቅድስት ቤርሳቤህ (ቤትስባ)4.ናቡቴ ኢይዝራኤላዊ5.አባ ዮሐንስ ሊቀ ዻዻሳት
=>ወርኀዊ በዓላት1.ልደታ ለማርያም ድንግል እግዝእትነ2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና3.ቅዱስ በርተሎሜዎስ ሐዋርያ4.ቅዱስ ሚልኪ ትሩፈ ምግባር5.ቅዱስ ራጉኤል ሊቀ መላእክት
=>+"+ ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌበኮሬብ ያዘዝኩትን: የባሪያየን የሙሴን ሕግ አስቡ::እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣነቢዩን ኤልያስን እልክላቹሃለሁ:: መጥቼም ምድርንበእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደልጆች: የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል:: +"+ (ሚል. 4:4)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

Untitled

✝✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳን "ሠለስቱ ደቂቅ" እና "አባ ሖር ገዳማዊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
" ታኅሣሥ 2 "
+*" ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ "*+
=>አናንያ: አዛርያና ሚሳኤልን እንዲያው በቀድሞው አጠራር ሠለስቱ ደቂቅ (ሦስቱ ሕጻናት) እንላቸዋለን እንጂ ለእኛስ በእድሜም: በጸጋም: በትሩፋትም አባቶቻችን ናቸው::
+ቅዱሳኑ የወቅቱ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጆች ናቸው:: ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ ሕዝቡን ሲማርክ አብረው ተማርከው ባቢሎን ወርደዋል::
+ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግስት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር:: ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ:: ምንም እንኩዋ በቤተ መንግስት ውስጥ ቢኖሩ: ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ::
+አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከነርሱ የሚደርስ አልተገኘም:: ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው:: ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው::
+ከነገር ሁሉ በሁዋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ:: ናቡከደነጾር 60 ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ ስገዱ ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው:: ነበልባሉ ከጉድጉዋዱ ወደ ላይ 49 ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም::
+ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልዐከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው:: ከሆነው ነገር የተነሳም አሕዛብ አፈሩ:: ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ::
+ከዚያች ቀን በሁዋላ አናንያ: አዛርያና ሚሳኤል በአት አጽንተው: በጾምና በጸሎት ተወስነው ኑረዋል:: ነፍሳቸው ከሥጋቸው ስትለይ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆኗል:: ቅዱስ ዳንኤልና ናቡከደነጾር ተሯሩጠው ቢሄዱ ሦስቱም በአንድነት ዐርፈው ተገኝተዋል:: ንጉሡ በእጅጉ ይወዳቸው ነበርና በወርቅ በተለበጠ ሳጥን ቀብሯቸዋል:: ስሞት ከመካከላቸው ቅበሩኝ በማለቱ ዛሬ ድረስ ለበቁ አባቶች የአራቱ መቃብር ባቢሎን ውስጥ ይታያል::
+ቅዱሳን አናንያ: አዛርያና ሚሳኤል (ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጐ) ያረፉት ግንቦት 10 ቀን ሲሆን ዘመኑም ከክርስቶስ 500 ዓመት በፊት ነው:: ይህቺ ዕለት ደግሞ ናቡከደነጾር ወደ እሳት ሲጥላቸው መልአከ እግዚአብሔር እነርሱን ያዳነበት ቀን ናት::
+አምላካቸው ከአሳት ባወጣቸው በዚህ ቀንም:-"ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ::ስቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ ለዓለም::" የሚለውን ምስጋና ፈጣሪ ገልጾላቸው ደርሰውታል:: በእሳቱ ውስጥ ሆነው ተናግረውታል::
+ድርሰታቸው 2 ወገን ሲሆን ባለ ስድስት አንቀጹ ምስጋናቸው ከ600 ዓመት በሁዋላ ክርስቶስ እንደሚወለድ የሚያሳይ ነው:: ሌላኛውና 33 አንቀጾች ያሉት ምስጋናቸው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለ33 ዓመታት እንደሚመላለስ ያጠይቃል::
+ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከ900 ዓመታት በሁዋላ (ማለትም ከክርስቶስ ልደት በ400 ዓመታት) ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ::
+ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ "አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?" አለው:: ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ:: በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ:: ሠለስቱ ደቂቅም "ወዳጃችን! ምን ሆንክ?" አሉት::
+ቅዱሱም መልሶ "ወደ ግብጽ እንሒድ:: አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋቹሃል" አላቸው:: እነሱም "ለቅዱሱ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው:: እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ:: ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም:: ለክብርህ ግን እንመጣለን::"
+"ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው" ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት:: ሐጺርም መጥቶ መልአክቱን አደረሰ:: በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን:- ቴዎፍሎስ: ቄርሎስ: ሐጺር ዮሐንስና ሌሎችም ከምዕመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ::
+እጅግ የሚደነቅ ብርሃንም ከበባቸው:: በብርሃኑ መካከል ሠለስቱ ደቂቅ ሲያልፉ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ሕዝቡም በደስታና በዝማሬ የቅዱሳኑን ቅዳሴ ቤት አክብሯል::
+"+ አባ ሖር ገዳማዊ +"+
=>በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን ከጻድቃንም: ከሰማዕታትም አሉ:: ከጻድቃኑ መካክል: በተለይም ከታላላቆቹ አንዱ ቅዱስ አባ ሖር ነው:: አባ ሖር በዘመነ ጻድቃን የነበረና በደግነቱ የሚታወቅ ክርስቲያን ነው::
+በዓለም ያለውን በጐነት ሲፈጽም ድንግልናውን እንደ ጠበቀ ገዳም ገባ:: በዚያም በአገልግሎት ተጠምዶ ዘመናትን አሳለፈ:: ከዚያም መነኮሰ:: ከመነኮሰ በሁዋላ ደግሞ አበውን በማገልገል: በጾምና በጸሎት: በበጐው ትሕርምት ሁሉ የተጠመደ ሆነ:: ግራ ቀኝ የማይል ("ጽኑዕ ከመ ዓምድ ዘኢያንቀለቅል" እንዲሉ አበው) ብርቱ ምሰሶ ሆነ::
+ሰይጣንም አባ ሖርን በብዙ ጐዳና ፈተነው:: ከእርሱ ጋር መታገል ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት በገሃድ ተገለጠለት:: "አንተኮ የምታሸንፈኝ በአበው መካከል ስለ ሆንክ ነው:: በበርሃ ብቻህን ባገኝህ ግን እጥልሃለሁ" ሲል ተፈካከረው::
+አባ ሖርም የዳዊትን መዝሙር እየዘመረ ጭው ወዳለ በርሃ ገባ:: በዚያም ሰይጣን ታገለው:: ግን ሊያሸንፈው አልቻለም:: ምክንያቱም ኃያሉ እግዚአብሔር ከጻድቁ ጋር ነበርና:: ሰይጣን እንደ ተሸነፈ ሲያውቅ እንደ ገና ሌላ ምክንያት ፈጠረ::
+አሁንም በገሃድ ተገልጦ ተናገረው:: "በዚህ በበርሃ ማንም በሌለበት ብታሸንፈኝ ምኑ ይደንቃል! ወደ ከተማ ብትሔድ ግን አትችለኝም" አለው:: ቅዱስ ሖር ግን አሁንም ሰይጣንን ያሳፍር ዘንድ በፈጣሪው ኃይል ተመክቶ ወደ ዓለም ወጣ::
+"እግዚአብሔር ያበርሕ ሊተ ወያድኅነኒ: ምንትኑ ያፈርሃኒ - እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው:: የሚያስፈራኝ ማነው!" ሲል (መዝ. 26:1) ይጸልይ ነበር:: በከተማም በነበረው ቆይታ አልባሌ ሰው መስሎ ደካሞችን ሲረዳ: ነዳያንን ሲንከባከብ: ለድሆች ውሃ ሲቀዳ: እንጨት ሲሰብር ይውልና ሌሊት እንደ ምሰሶ ተተክሎ ሲጸልይ ያድራል::
+ሰይጣን በዚህም እንዳላሸነፈው ሲያውቅ ከሰዎች ጋር በሐሰት ሊያጣላው ሞከረ:: ፈረስ ረግጦ የገደለውን አንድ ሕጻን ሲያይ ሰይጣን ሰው መስሎ ወደ አባ ሖር እየጠቆመ "እርሱ ነው ረግጦ የገደለው" አላቸው:: የሕጻኑ ወገኖች ቅዱሱን ሲይዙት አባ ሖር "ቆዩኝማ" ብሎ የሞተውን ሕጻን አንስቶ ታቀፈው::
+ጸልዮ በመስቀል ምልክት አማተበበትና "እፍ" ቢልበት ሕጻኑ ከሞት ተነሳ:: ለወላጆቹም ሰጣቸው:: ይሕንን ድንቅ የተመለከቱ የእስክንድርያ ሰዎችም ይባርካቸው ዘንድ ሲጠጉት ተሰውሯቸው በርሃ ገባ:: ውዳሴ ከንቱን ፈጽሞ ይጠላት ነበርና::
+ጻድቁ አባ ሖር ቀሪ ዘመኑን በበርሃ አሳልፎ በዚህች ቀን በክብር ዐርፏል::
=>አምላከ ጻድቃን ቅዱሳን ከነደደ እሳት: ከዲያብሎስ ክፋትም ይሰውረን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
=>ታሕሳስ 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=1.ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ (አናንያ: አዛርያ: ሚሳኤል)2.አባ ሖር ጻድቅ3.ቅዱስ አውካቲዎስ ሰማዕት4.አባ አንበስ ሰማዕት5.7,033 ሰማዕታት (የቅዱስ ፋሲለደስማሕበር)6.ቅዱስ ናትናኤል መነኮስ
=>ወርኀዊ በዓላት1.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)2.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ3.ቅዱስ አቤል ጻድቅ4.ቅዱስ አባ ዻውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)5.ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይ (መጥምቀ መለኮት)6.ሊቁ አባ ሕርያቆስ7.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
=>+"+ ናቡከደነፆርም መልሶ:- 'መልአኩን የላከ: ከአምላካቸውም በቀር ማንንም አምላክ እንዳያመልኩ: ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን: የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን: በእርሱ የታመኑትን ባርያዎቹን ያዳነ: የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ::' +"+ (ዳን. 3:28)
✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞

Untitled

†††✝ እንኳን ለእግዝእትነ ማርያም (#በዓታ): አቡነ ዜና ማርቆስ ጻድቅ እና ቅዱስ ፋኑኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም †††
††† ከነገደ ይሁዳ የሚወለድ ቅዱስ ኢያቄም የሚባል ደግ ሰው ከነገደ ሌዊ (አሮን) የተወለደች ሐና የምትባል ደግ ሴት አግብቶ በሕጉ ጸንተው: በሥርዓቱ ተጠብቀው ይኖሩ ነበር:: ነገር ግን በዘመኑ ሰዎች "ልጅ የላችሁም" በሚል ይናቁ ነበር::
ኦሪታውያን ልጅ የሌለውን "ኅጡአ በረከት-ከጸጋ እግዚአብሔር የራቀ" ነው ብለው ያምኑ ነበር:: ኢያቄምና ሐና ልጅ እንዲሰጣቸው ሲያዝኑ: ሲጸልዩ ዘመናቸው አልፎ አረጁ:: እነሱ ግን የሚያመልኩት የአብርሃምና ሣራን አምላክ ነውና ተስፋ አልቆረጡም::
የለመኑትን የማይነሳ ጌታ በስተእርጅናቸው ድንቅ ነገርን አደረገላቸው:: አንድ ቀን እርግቦች ከጫጩቶቻቸው ጋር ሲጫወቱ የተመለከተች ቅድስት ሐና ፈጽማ አለቀሰች:: "እንስሳትና አራዊትን: እጽዋትን ሳይቀር በተፈጥሯቸው እንዲያፈሩ የምታደርግ አምላክ ምነው ሐናን ድንጋይ አድርገህ ፈጥረሃታልን?" ብላ አዘነች::
ይህን የተመለከተ ቅዱስ ኢያቄም ወደ ተራራ ወጥቶ ሱባኤ ያዘ:: ለ40 ቀናትም ሲጸልይና ሲማለል ቆየ:: በ40ኛው ቀን ሁለቱም ሕልምን ያልማሉ::እርሱ:-*ነጭ ርግብ ሰማያትን ሰንጥቃ ወርዳ: በሐና ቀኝ ጀሮ ገብታ: በማሕጸኗ ስትደርስ አየ::
እርሷ ደግሞ:-*የኢያቄም በትር አብቦ: አፍርቶ: ጣፋጭ ፍሬውን ሰው ሁሉ ሲመገበው ታያለች:: ቅዱስ ኢያቄም ከሱባኤ እንደ ተመለሰ ያዩትን ተጨዋውተው "ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን" አሉ:: ለ7 ቀናትም በጋራ እግዚአብሔርን ሲለምኑ ሰነበቱ::
በ7ኛው ቀን (ማለትም ነሐሴ 7) መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ክንፉን እያማታ ወደ እነርሱ ወረደ:: "ዓለም የሚድንባት: የፍጥረት ሁሉ መመኪያ የሆነች ልጅ ትወልዳላችሁ" ብሏቸው ተሠወራቸው:: እነርሱም ደስ ብሏቸው እግዚአብሔርን አመሰገኑ::
እንደ ሥርዓቱም አብረው አድረው እመ ብርሃን ተጸነሰች::"ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተጸነስኪ . . .ድንግል ሆይ! ኃጢአት ባለበት ሥጋዊ ፍትወት የተጸነስሽ አይደለም" እንዳለ ሊቁ:: (ቅዳሴ ማርያም)
††† "ለጽንሰትኪ በከርሥ::እንበለ አበሳ ወርኩስ::ወለልደትኪ እማሕጸን ቅዱስ . . .""ድንግል ሆይ! መጸነስሽ ያለ በደል (ያለ ጥፋት) ነው: የተወለድሽበት ማሕጸንም ቅዱስ ነው . . ." (መጽሐፈ ሰዓታት፣ ኢሳ. 1:9)"ኢያቄም ወሐና ወለዱ ለነ ሰማየ::ሰማዮሙኒ አስረቀት ለነ ፀሐየ::""ኢያቄምና ሐና ሰማይን ወለዱልን::ሰማያቸው ደግሞ ፀሐይን አወጣችልን (ወለደች-አስገኘችልን)"
የዓለማችን ወላጆች ነቢያት ሐዋርያትን: ጻድቃን ሰማዕታትን ወልደው ከብረዋል: ተመስግነዋል:: ኢያቄምና ሐና ግን ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ቢሰበሰብ በእግሯ የረገጠችውን ትቢያ እንኳ መሆን የማይችል: የሰማይና የምድር ንግሥት: የእግዚአብሔርን እናት: እመቤታችን ማርያምን ወለዱልን::
ኢያቄም ወሐና ለእግዚአብሔር የሥጋዌ አያቶቹም ተባሉ:: ቅዱሳኑ እስኪያረጁ ድረስ በመካንነት አዝነው ፀልየዋል:: ንጽሕናቸውና ደግነታቸው ተመስክሮላቸው ድንግል ማርያምን አግኝተዋል::
እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተጸንሳ ግንቦት አንድ ቀን ተወልዳለች:: ከአዳም ስሕተት በኋላ ያለ ጥንተ አብሶ የተወለደች የመጀመሪያዋ ሰው ድንግል ማርያም ሆናለች:: (ኢሳ. 1:9)
††† የእመቤታችን የዘር ሐረግ:-*አዳም-ኖኅ-አብርሃም-ይስሐቅ-ያዕቆብ=*በእናቷ:-ሌዊ-ቀዓት-እንበረም-አሮን-ቴክታና በጥሪቃ-ሔኤሜን-ዴርዴን-ቶና-ሲካር-ሔርሜላና ማጣት-ሐና::
*በአባቷ በኩል:-ይሁዳ-ፋሬስ-ሰልሞን-ቦኤዝ-እሴይ-ዳዊት-ሰሎሞን-ሕዝቅያስ-ዘሩባቤል-አልዓዛር-ቅስራ-ኢያቄም ይሆናል::
ለጨለማው ዓለም የብርሃን መቅረዝ ሆና ትጠቅመን ዘንድ: አንድም ትንቢቱና ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም: በሊባኖስ ተራራ ከ2,023 ዓመታት በፊት ተወልዳለች::
ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ድንግል እመ ብርሃንን ከወለዱ በኋላ ለ3 ዓመታት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ: ነዳያንንም ሲጠግኑ ኖሩ:: በእነዚህ ዓመታትም ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከእቅፏ አውርዳት አታውቅም::
ቅዱሳን መላእክትም ዘወትር እየመጡ ያጫውቷት ይንከባከቧትም ነበር:: 3 ዓመት በሞላት ጊዜም በቅድስት ሐና አሳሳቢነት ብጽዓታቸውን (ስዕለታቸውን) ይፈጽሙ ዘንድ ተዘጋጁ::
እንደ ሥርዓቱ የሚዘጋጀውን (መባውን) ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ ሲደርሱ አበው ካህናትና የመቅደሱ አገልጋዮች ሁሉ ሊቀበሏቸው ወጡ:: ሕዝቡ: ሊቃነ ካህናት ቅዱሳን ዘካርያስና ስምዖን: ኢያቄም ወሐና ከድንግል ማርያም ጋር ቆመው ሳሉም ሊቀ መላእክት ፋኑኤል ከሰማይ ወርዶ ረቦ ታየ::
ከቅዱስ ዘካርያስ ጀምሮ ሁሉም ሰው ሕብስትና ጽዋዑን ለመቀበል ቀረበ:: ግን መልአኩ ራቀ:: ድንግል ማርያም በቀረበች ጊዜ ግን ከመሬት አፈፍ አድርጐ አንስቶ: ክንፉን ጋርዶ ሰማያዊውን ማዕድ መገባት:: በዚህ ደስ የተሰኙ ካህናትና ሕዝቡ እየዘመሩ በታኅሣሥ ሦስት ቀን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብተዋታል::
አማናዊት መቅደሰ መለኮት ድንግል ማርያም ወደ ኦሪቱ ቤተ መቅደስ በገባችበት ዕለት ጸሎታችን እንድትሰማን እንደ ሊቃውንቱ:-"ማርያም አንቲ ሰዋስው ዘምድረ ሎዛ::ዲቤኪ ትዕርግ ጸሎትየ ከመ ጼና ሠናይ መዓዛ::ኀበ ለነፍስየ ታሰስል ትካዛ" እንላለን:: (አርኬ)
††† አቡነ ዜና ማርቆስ ጻድቅ †††
††† አባ ዜና ማርቆስ በሃገራችን በተለይ በደቡብ ምድረ ጉራጌ ስመ ጥር ሐዋርያዊ ጻድቅ ናቸው:: ምድረ ሽዋ ደግሞ እርሳቸውን ጨምሮ የብዙ ቅዱሳን መፍለቂያ ናትና ክብር ይገባታል:: ነቢየ ጽድቅ ዳዊት "ትውልደ ጻድቃን ይትባረኩ-የጻድቃን (የቅኖች) ትውልድ ይባረካል" (መዝ. 111) ያለው ነገር በምድረ ዞረሬ (ጽላልሽ) ተፈጽሟል::
ሦስት ወንድማማች የተባረኩ ካህናት በስፍራው ነበሩ:: ስማቸው ጸጋ ዘአብ: እንድርያስና ዮሐንስ ይባላል:: ከእነዚህ መካከልም ጸጋ ዘአብ: እግዚእ ኃረያን አግብቶ ኮከበ ከዋክብት ተክለ ሃይማኖትን ሲወልድ ካህኑ ዮሐንስ ደግሞ ዲቦራ የምትባል ደግ ሴት አግብቶ ዜና ማርቆስን ወልዷል::
የአቡነ ዜና ማርቆስ ጽንሰታቸው ሚያዝያ 30 በብሥራተ ማርቆስ ወንጌላዊ ሲሆን ልደታቸው ደግሞ ኅዳር 24 ቀን በበዓለ ሱራፌል ካህናተ ሰማይ ነው:: ዘመኑም 13ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው::
ዜና ማርቆስ በተወለዱ በ40 ቀናቸው አጐታቸው ቀሲስ እንድርያስ (የ72 ዓመት ሽማግሌ ናቸው) ሊያጠምቁ ቀረቡ:: ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን ከእናታቸው እቅፍ ወርደው 3 ጊዜ "እሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ" እያሉ ቢሰግዱ የመጠመቂያው ገንዳ ውኃ ፈላ::
ይህንን የተመለከቱት ካህኑ ደንግጠው ወጥተው ሲሮጡ ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት ተገልጦ "አትፍራ! ይልቁኑ ከጠበሉ ራስህን ተቀባ" አላቸው:: እንዳላቸው ቢያደርጉ ራሰ በራ ነበሩና ጸጉር በቀለላቸው::
ሕጻኑ ዜና ማርቆስ ግን 5 ዓመት ሲሞላቸው ወደ ጉባኤ ቤት ገብተው በአጭር ጊዜ ብሉይ ከሐዲስ ጠነቀቁ:: ዲቁናን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱም ሽፍቶች አግኝተው: በትራቸውን ቀምተው: አንገላተው ሰደዋቸዋል::
ወዲያው ግን ያቺ በትር እባብ ሁና ሽፍቶችን አጥፍታቸዋለች:: ጻድቁ ለቤተሰብ እየታዘዙ: ንጽሕናቸውንም እየጠበቁ ኑረው 30 ዓመት ሲሞላቸው ወላጆቻቸው ግድ ብለው ማርያም ክብራ ለምትባል ወጣት አጯቸው::
እሳቸው ግን በሠርጉ ሌሊት ከጫጉላ ቤት ጠፍተው በርሃ ገቡ:: ከዚያም በቅዱስ መልአክ መሪነት ሃገረ ምሑር ደረሱ:: በቦታውም ጣዖትን ሰባብረው: ተአምራትንም አድርገው: ሕዝቡን ወደ ክርስትና መለሱ:: መስፍኑ አውጊት ግን ተፈታተናቸው: አሠራቸው: አሥራባቸው::
በጦር እወጋለሁ ሲል ግን መሬት ተከፍታ ከነ ተከታዮቹ ውጣዋለች:: ከ5 ዓመታት በኋላ ግን ማልደው: ከሰጠመበት አውጥተው አጥምቀውታል:: ቀጥለውም ምድረ ጉራጌ ወርደው: ሕዝቡን አሳምነው አጥምቀዋል::
የአዳልን ሕዝብና ንጉሡን አብደልማልን አስተምረው ያጠመቁም እርሳቸው ናቸው:: ድል አሰግድ የሚባለውን መስፍንም ያሳምኑ ዘንድ ጠንቅዋዮቹን ድል አድርገው አጥፍተዋል::
ጻድቁ ዜና ማርቆስ ከዚህ ሐዋርያዊ ሥራቸው በተጨማሪ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምንኩስናን ከተቀበሉባት ቀን ጀምረው በጾም: በጸሎትና በሰጊድ ኑረዋል:: ፀሐይን በምድረ ጉራጌ እስከ ማቆም ደርሰውም ብዙ ተአምራትን ሠርተዋል::
አእላፍ ደቀ መዛሙርትን ሲያፈሩ 200 አንበሶች በቀኝ: 200 ነብሮች በግራ ይከተሏቸው ነበር:: ደብረ ብሥራትን ጨምሮም ገዳማትን አንጸዋል:: በመጨረሻም የምሕረት ቃል ኪዳንን ከፈጣሪ ዘንድ ተቀብለው ታኅሣሥ ሦስት ቀን በ140 ዓመታቸው ዐርፈዋል::
††† የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን::
††† ታኅሣሥ 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም2.ብጹዓን ኢያቄም ወሐና3.ቅዱሳን ካህናት ዘካርያስና ስምዖን4.ቅዱስ ፋኑኤል ሊቀ መላእክት5.አቡነ ዜና ማርቆስ ጻድቅ
††† ወርኀዊ በዓላት1.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ጻድቅ (ዘደብረ በንኮል)2.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ3.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)
††† "ድንግል ሆይ! አንገታቸውን እንደሚያረዝሙ እንደ እብራውያን ሴቶች ልጆች በዋዛ ያደግሽ አይደለሽም:: በቅድስናና በንጽሕና በቤተ መቅደስ ኖርሽ እንጂ::ድንግል ሆይ! ምድራዊ ሕብስትን የተመገብሽ አይደለም:: ከሰማየ ሰማያት የበሰለ ሰማያዊ ሕብስትን እንጂ::ድንግል ሆይ! ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም:: ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ሰማያዊ መጠጥን እንጂ::" †††(ቅዳሴ ማርያም)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

Untitled

✝✝††† እንኳን ለቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
†††በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ✝✝ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ ✝✝†††
††† ቅዱሱ ሐዋርያ ተወልዶ ያደገው በቤተ ሳይዳ አካባቢ ሲሆን የሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ትንሽ ወንድም ነው:: አባቱም ዮና ይባላል:: ገና ከልጅነቱ ጀምሮ አሣ ማጥመድን ከትልቅ ወንድሙ ተምሯል:: እድሜው ከፍ ባለ ጊዜ ኦሪትን ተምሮ የመጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆኗል::
ከእርሱም እያገለገለ ለ6 ወራት ተምሯል:: በወቅቱ ከወንጌላዊው (ወልደ ዘብዴዎስ) ዮሐንስ ጋር ቅርብ ባልንጀራም ነበር:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ያን ድንቅ ምሥጢረ ሥላሴ ከተመለከቱትም አንዱ ነው::
ጌታ ከጾም (ከገዳመ ቆረንቶስ) በተመለሰ ጊዜ እንድርያስ መንፈስ ቅዱስ አነሳስቶት ተከትሎታል:: መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ "ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘያዐትት ኃጢአተ ዓለም - የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ እነሆ" ማለቱን ሰምቶ ቅዱስ እንድርያስ ጌታን ተከተለ::
በዚህም የመጀመሪያው የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመባል በቃ:: (ዮሐ. 1:47) ሊቁ ማር ገላውዴዎስም እመቤታችንን ሲያመሰግናት:-"ለሐዋርያ እንድርያስ ቀዳማዊ ማርያም ሃይማኖቱ::(ለመጀመሪያው ሐዋርያ ለእንድርያስ ሃይማኖቱ ማርያም አንቺ ነሽ)" ብሏል:: (መልክዐ ስዕል)
ቅዱሱ ሐዋርያ ስሉጥ (ፈጣን) አገልጋይ እንደ ነበርም ወንጌል ይነግረናል:: (ዮሐ. 6:9, 12:22) ለ3 ዓመታት ከ3 ወራት ከጌታ እግር ሥር ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሎ ምን ሃገረ ስብከቱ ልዳ ብትሆን ብዙ አሕጉረ ዓለምን ሰብኳል::
ሐዋርያው ከጌታ ጋር በመርከብ ውስጥ ተነጋገረና ቅዱስ ማትያስን ሰውን ከሚበሉ ሰዎች እጅ አዳነ:: ቅዱስ እንድርያስ 30 ቀናት የሚፈጅ የባሕር ላይ ጉዞ ለማድረግ ከአርድእቱ ጋር ወደ ወደብ ቢሔድም መርከበኞች ሁሉ አናሳፍርም በማለታቸው የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣት መርከበኛ መስሎ ሐዋርያውንና አርድእቱን የሠላሳውን ቀን መንገድ በሰዓታት ልዩነት እንዲጨርሱ አድርጓል::
ቅዱስ እንድርያስም እንዲሁ ሰው መስሎት ለጌታችን ስለ ጌታችን ሰብኮለታል:: መርቆታልም:: መርከበኛው ጌታችን መሆኑን ሲያውቅም ደንግጦ አልቅሷል::
¤"ሶበ አእመረ ኪያሁ ወጠየቀ አምሳሎ::ዘተናገርኩ በድፍረት ምስሌከ ኩሎ::ሥረይ ሊተ ጌጋይየ ወኅድግ ይቤሎ::" እንዲል "ማረኝ?" ብሎታል:: ጌታችንም "አይዞህ እኔ ካንተ ጋር ነኝ" ብሎታል::
እንድርያስ ማለት "ተባዕ" (ደፋር: ብርቱ) ማለት ነው:: ድፍረት ሥጋዊ: ድፍረት መንፈሳዊ አለና:: "ድፍረት ሥጋዊ" በራስ ተመክቶ ሌሎችን ማጥቃት: ለጥቃትም ምላሽ መስጠት ነው::
"ድፍረት መንፈሳዊ" ስለ ክርስቶስ: ስለ ቀናችው ሃይማኖት ሲሉ በራስ ላይ መጨከን: ራስን አሳልፎ መስጠት: መከራንም አለመሰቀቅ ነው:: ይሕንንም አበው "ጥብዓት" ይሉታል::
ቅዱስ እንድርያስም ለጊዜው በቤተ እሥራኤል መካከል ደፋር የነበረ ሲሆን ለፍጻሜው ግን እስከ ሞት ደርሶ ስመ ክርስቶስን በድፍረት ገልጧልና "ተባዕ (ደፋር)" ይለዋል::"ዘኢያፍርሃከ ምንተ መልአከ ዓመጻ ጽኑዕ::አንተኑ እንድርያስ ተባዕ" እንዲል:: (መልክዐ ዓቢየ እግዚእ)
የቅዱስ እንድርያስ ሃገረ ስብከቱ ልዳ (ልድያ) ናት:: ይህቺን ሃገር: አስቀድሞ ሊቀ ሐዋርያቱ (ትልቅ ወንድሙ) ቅዱስ ጴጥሮስ አስተምሮባታል:: ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ሮም ሲዘልቅ ቅዱስ እንድርያስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ገብቶ ብዙ ደክሞባታል::
በቀደመው ዘመን ልዳ እንደ ዛሬው ትንሽ ሃገር አልነበረችም:: ቅዱሱ ሐዋርያ ወደ ቦታው ገብቶ: ስመ ክርስቶስን ሰብኮ ብዙዎችን ቢያሳምንም የጣዖቱ ካህናት ግን ተበሳጩ:: በእርግጥ እነርሱ የሚያጥኗቸው ድንጋዮች አማልክት እንዳልሆኑ ጠንቅቀው ያውቃሉ::
ነገር ግን ከብረው: ገነው: ባለ ጠጐችም ሆነው የሚኖሩበት ሐሰት እንዲገለጥ አይፈልጉምና እውነትን ከመቀበል ሐዋርያቱን ማሳደዱን ይመርጡ ነበር:: አሁንም የልዳ ከተማ ሕዝብ ማመናቸውን ሲሰሙ በቁጣ ሠራዊት ሰብስበው: ጦርና ጋሻን አስታጥቀው: ሐዋርያውን ያጠፉ ዘንድ እየተመሙ መጡ::
ቅዱስ እንድርያስ ይህንን ሲያውቅ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል "ጥዑመ-ቃል" የሚባለውን ቅዱስ ፊልሞናን (ኅዳር 27 ቀን ያከበርነውን ማለት ነው) ጠርቶ የቅዱስ ዳዊትን መዝሙር ገልጦ ምዕራፍ (113:12) ላይ ሰጠውና "ጮክ ብለህ አንብብ" አለው::
††† ቅዱስ ፊልሞናም በቅዱስ መንፈሱ ተቃኝቶ ያነብ ጀመር::"አማልክቲሆሙ ለአሕዛብ ዘወርቅ ወዘብሩር::ዓይን ቦሙ ወኢይሬእዩ::እዝን ቦሙ ወኢይሰምዑ::አንፍ ቦሙ ወኢያጼንዉ . . .የአሕዛብ አማልክት ከወርቅና ከብር የተሠሩ ናቸው::ዓይን አላቸው: ግን አያዩም::ጆሮ አላቸው: ግን አይሰሙም::አፍንጫ አላቸው: ግን አያሸቱም . . ." አለ::
በፍጻሜውም "ከማሁ ለይኩኑ ኩሎሙ እለ ገብርዎሙ / የሚሰሯቸው ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ" ብሎ ጸጥ አለ:: ይህንን የሰሙት ካህናተ ጣዖትና ሠራዊታቸው የልባቸው መታጠቂያ ተፈታ:: በደቂቃዎችም የመንፈስ ቅዱስ ምርኮኛ ሆነው በቅዱስ እንድርያስ ፊት ሰገዱ::
እርሱም አጥምቆ ወደ ምዕመናን ማኅበር ቀላቀላቸው:: አንድ ጊዜ ደግሞ ከልዳ አውራጃዎች በአንዱ እንዲህ ሆነ:: በጨዋታ ላይ ሳሉ የክርስቲያኑ ልጅ የአሕዛቡን ቢገፈትረው ወድቆ ሞተ::
የሟቹ አባትም የገዳዩን አባት ዮሐንስን (ቀሲስ ነው) "ልጅህን በፈንታው እገድለዋለሁ" አለው:: ቀሲስ ዮሐንስ ግን "ለመምሕሬ ለእንድርያስ እስክነግር ድረስ ታገሠኝ" ብሎ ሒዶ ለሐዋርያው ነገረው::
በወቅቱ ቅዱስ እንድርያስ የወንጌል አገልግሎት ላይ ስለ ነበር ቅዱስ ፊልሞናን ላከው:: ፊልሞና ወደ አካባቢው ሲደርስ ሁከት ተነስቶ አገረ ገዢው ሕዝቡን ይደበድብ ነበርና ቀርቦ ገሠጸው:: "የተሾምከው ሕዝቡን ልታስተዳድርና ልትጠብቅ ነው እንጂ ልታሰቃይ አይደለም" ስላለው አገረ ገዥው ቅዱሱን አሰቀለው::
ተሰቅሎም ሳለ ይገርፉት ነበርና አለቀሰ:: ምክንያቱም ቅዱስ ፊልሞና ሕጻን ነበርና:: በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ሲያለቅሱለት ቁራ: ወፍና ርግብ ቀርበው አጽናኑት:: ከእነርሱም መርጦ ርግብን ወደ ቅዱስ እንድርያስ ላካት::
ርግብ በሰው ልሳን ስትናገር የሰማት አገረ ገዢው ተገርሞ ቅዱሱን ከተሰቀለበት አወረደው:: ሰይጣን ግን በብስጭት በመኮንኑ ሚስት አድሮ ልጁን አስገደለበት:: በሃዘን ላይ ሳሉም ቅዱስ እንድርያስ ደረሰ::
በመኮንኑ ሚስት ያደረውን ሰይጣንን ወደ ጥልቁ አስጥሞ የሞተውን አስነሳው:: መጀመሪያ የሞተውን ሕጻን ደግሞ ፊልሞና አስነሳው:: በእነዚህ ተአምራትም መኮንኑ: ሕዝቡና ሠራዊቱ በክርስቶስ አምነው ተጠመቁ::
ቅዱስ እንድርያስ በእድሜው የመጨረሻ ዘመናት ከልድያ ወጥቶ በብዙ አሕጉራት አስተማረ:: ስሟ ባልተጠቀሰ አንዲት ሃገር ውስጥ ግን በእሳት ሊያቃጥሉት ሲሉ እሳት ከሰማይ ወርዳ በላቻቸው::
ድጋሚ ሌሎች ይዘው አሰሩት: ደበደቡት አሰቃዩት:: በሌሊትም ጌታ መጥቶ አጽናናው:: ታኅሣሥ 4 ቀን በሆነ ጊዜም ወደ ውጭ አውጥተው: ወግረውና ሰቅለው ገድለውታል::
¤እኛም እንደ አባቶቻችን:-"እዜምር ለከ ወእየብብ በሃሌ ሉያ::አንቅሃኒ እምሐኬትየ እንድርያስ ሐዋርያ::ከመ በእዴከ ነቅሐት እሙታን ልድያ::" እያልን ቅዱሱን እንጠራዋለን:: (አርኬ ዘታኅሣሥ 4)††† አምላከ ቅዱስ እንድርያስ ከሞተ ልቡና አንቅቶ ለክብሩ ያድርሰን:: ከበረከቱምያድለን::
††† ታኅሣሥ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት1.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ2.አባ ጻዕ3.አባ ያዕቆብ4.ቅድስት ታኦድራ
††† ወርኀዊ በዓላት1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ2.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት3.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ (ሰማዕት)
††† "ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ጌታ ኢየሱስን ተከተሉት:: ጌታ ኢየሱስም ዘወር ብሎ: ሲከተሉትም አይቶ:- "ምን ትፈልጋላችሁ?" አላቸው:: እነርሱም:- "ረቢ ወዴት ትኖራለህ?" አሉት:: ትርጓሜው "መምህር ሆይ!" ማለት ነው:: "መጥታችሁ እዩ" አላቸው:: መጥተው የሚኖርበትን አዩ:: በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ:: አሥር ሰዓት ያህል ነበረ:: ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ::" †††(ዮሐ. ፩፥፴፯-፵፩)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††

Untitled

✝✝✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
✞✞✞ እንኩዋን ለእናታችን "ቅድስት አውጋንያ" : "አባ ገብረ ናዝራዊ" እና "ቅዱስ ፊቅጦር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
+*" ቅድስት አውጋንያ "*+
=>ይህቺ ቅድስት ወጣት ስም አጠራሯ በእውነት የከበረ ነው:: ዜና ሕይወቷ ሲሰማ ጣዕመ ነፍስን ያድላልና:: በፈጣሪ ረዳትነት ልጀምር:: እናንተም በእግዚአብሔር አጋዥነት ተከተሉኝ::
+ቅድስት አውጋንያ የ3ኛው መቶ ክ/ዘ የክርስትና ፍሬ ናት:: በትውልዷ ሮማዊት ስትሆን አባቷ ፊልዾስ ይባላል:: ሥራውም የጦር መሪ: የሃገርም አስተዳዳሪ ነው:: በስም ያልተጠቀሰች እናቷ ደግሞ ክርስቲያን ነበረች::
+ዘመኑ አስከፊ ሰለ ነበር (ለክርስቲያኖች ማለቴ ነው) ክርስትናዋን ደብቃ: አልባሌ (አሕዛባዊ) መስላ ትኖር ነበር:: ቅድስት አውጋንያን ስትወልድ ግን ጨነቃት:: እንዳታስጠምቃት የእርሷም ሆነ የሕጻን ልጇ እጣ ፈንታ ሞት መሆኑ ነው::
+ምክንያቱም ባሏ ፊልዾስ ክርስትናን ፈጽሞ የሚጠላ ጣዖት አምላኪ ነበርና:: ከዚያም አልፎ ሰዎች ለጣዖት እንዲንበረከኩም ያስገድድ ነበር:: ስለዚህ እናት ልጇን ሳታስጠምቅ: ግን በፍጹም የክርስትና ትምሕርትና ሥርዓት አሳደገቻት::
+ቅድስት አውጋንያም ጾምን ጸሎትን: ትሕትናን: ትእግስትን የተመላች ወጣት ሆነች:: ግን ምሥጢረ ጥምቀትን ታገኝ ዘንድ ዘወትር ፈጣሪዋን ትማጸን ነበር::
+በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉም አንድ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ:: መኮንኑ አባቷ (ፊልዾስ) በምድረ ግብጽ እስክንድርያ አገረ ገዥ ሆኖ በመሾሙ ጉዋዛቸውን ጠቅልለው ወረዱ:: ምንም ይህ ለቅድስት አውጋንያ መልካም አጋጣሚ ቢሆንም ሌላ ፈተናን አመጣባት::
+አባቷ ለአረማዊ መኮንን ሊድራት መሆኑን ሰማች:: አሁን ግን መቁረጥ ያስፈልግ ነበርና ወሰነች:: ወደ አባቷ ገብታም "አባቴ! አንድ ነገር ላስቸግርህ:: አንተ ለምትለኝ ሁሉ እታዘዛለሁ:: ግን ከሠርጌ ቀን በፊት ለአንዲት ቀን በዱር ውስጥ ተናፍሼ: ተዝናንቼ እንድመጣ ፍቀድልኝ?" አለችው::
+ምን እንዳሰበች ያልጠረጠረ አባቷም ከ2 ጃንደረቦች ጋር እንድትሔድ አደረገ:: በርሃ አካባቢ ሲደርሱም ቅድስት አውጋንያ እውነቱን ለ2ቱ ጃንደረቦች ተከታዮቿ ነገረቻቸው::
+"እኔ ወደ በርሃ የምሔደው ክርስቲያን ልሆን: ደግሞም ልመንን ነውና ካላሰኛችሁ ተመለሱ" አለቻቸው:: 2ቱም ግን በአንድ ቃል "ሞታችንም: ሕይወታችንም ከአንቺ ጋር ነው" ብለዋት አብረው ገዳም ገቡ::
+እንደ ደረሱም ምሥጢራቸውን ለአንድ ጻድቅ መነኮስ ተናግራ እንዲያጠምቃት ጠየቀችው:: መነኮሱም 3ቱንም ካጠመቃቸው በሁዋላ ቅድስት አውጋንያ "አመንኩሰን" ብትለው "ልጄ! ይሔ የወንዶች ገዳም ነውኮ" አላት::
+"አባ! ግድ የለህም! እኔ ራሴን እሰውራለሁ" አለችው:: ከዚያም ሥርዓተ ገዳምን አስተምሮ ስሟን "አባ አውጋንዮስ" ብሎ ከማሕበረ መነኮሳቱ ቀላቀላት:: *አውጋንያን *ታኦድራ *አንስጣስያ . . . የመሳሰሉ ስሞች በቀላል መንገድ ወደ ወንድ ስምነት *አውጋንዮስ *ቴዎድሮስ *አንስጣስዮስ . . .በሚል መቀየር ይችላሉና::
+ከዚህች ዕለት ጀምራ ቅድስት አውጋንያ በአባ አውጋንዮስነቷ ተጋድሎን ጀመረች:: ቀን ቀን ወንዶች መነኮሳት የሚሠሩትን ከባድ ሥራ ሁሉ ስትሠራ ትውልና ሌሊት በትጋት ስትጸልይ ታድራለች:: ለ1 ዓመት ያህል በፍጹም ተጸምዶ ገዳሙን አገለገለች::
+በነዚህ ጊዜያት የመጡባትን ፈተናዎችም ታገሰች:: ዓለምን የናቀችለት: የአባቷን ቤተ መንግስት የተወችለት ክርስቶስ ኃይሏ ነበርና:: በዚያ ሰሞንም የገዳሙ አበ ምኔት በማረፉ መነኮሳትን የሚመራና የሚናዝዝ ሌላ አበ ምኔትን ለመምረጥ ሱባኤ ገቡ::
+ከሱባኤ ወጥተው ሲሰበሰቡ ግን ያመጡት የመንፈስ ቅዱስ መልእክት የሚገርም ነበር:: የሁሉም ዓይን ወደ አባ አውጋንዮስ ተወረወረ:: እርሷ ምሥጢሯን (ሴትነቷን) ታውቃለችና ደነገጠች:: ምርጫው ግን የመንፈስ ቅዱስ ነበርና ግድ ብለው በእነዛ ሁሉ መነኮሳት ላይ እረኛ ሁና ተሾመች::
+በእርግጥ እርሷ ሴት በዚያውም ላይ ወጣት ናት:: ግን እውነተኛ የክርስቶስ ወዳጅ ነበረችና በፍጹም ትጋት መነኮሳትን አስተዳደረች:: ጸጋው ቢበዛላት የተጨነቀውን ታረጋጋ: የታመመውን እጇን እየጫነች በጸሎቷ ትፈውስ ነበር:: በዚህም መነኮሳቱ ደስ ተሰኙ::
+እርሷ ግን ስለዚህ ፈንታ ብዙ ፈተናዎችን በአኮቴት ታሳልፍ ነበር:: ስም አጠራሯም ከበርሃ ወጥቶ ወደ ከተሞች በመግባቱ ድውያን እየመጡ ከእርሷ ዘንድ ይፈወሱ ነበር:: አንድ ቀን ግን ያልተጠበቀ ፈተና መጣባት::
+አንዲት ሰይጣን ያደረባትን ሴት ካዳነቻት በሁዋላ: መልኩዋ እጅግ ውብ ስለ ነበር የዝሙት ጥያቄን አቀረበችላት:: (ሴቷ ለሴቷ ማለት ነው) ለእርሷ ወንድ መስላታለችና:: ቅድስት አውጋንያ ግን ገሥጻ ሰደደቻት:: በዚህ የበሸቀችው ያቺ ክፉ ወጣት ወደ ከተማ ሒዳ ለሃገረ ገዢው ፊልዾስ (የቅድስቷ አባት) ክስ አቀረበች::
+እርሱ (ፊልዾስ) አውጋንያ ከጠፋችበት ቀን ጀምሮ በስሟ ጣዖት አሠርቶ የሚሰግድ ሆኖ ነበር:: ወጣቷ "በገዳም ያሉ መነኮሳት: በተለይ አውጋንዮስ የሚሉት መሪያቸው አስገድዶ ከክብር ሊያጐድሉኝ ሲሉ አመለጥኩ" ብላ በሃሰት በመክሰሷ ገዳሙ እንዲመዘበር: መነኮሳቱም እንዲገረፉ መኮንኑ ፊልዾስ አዘዘ::
+በግርፋቱ መካከልም ብዙ መነኮሳት ሞቱ:: የእነርሱ ስቃይ ያንገበገባት ቅድስት አውጋንያ ግን አባቷን ለብቻ ወስዳ አስምላ ማንነቷን ገለጸችለት:: የናፈቃት ልጁን ሲያገኝ ደስ ብሎት መነኮሳቱን እንዲተዉ አዘዘ::
+ለብቻ ከልጁ ጋር ተቀምጦም ያለፈውን ነገር ሁሉ ነግራ ስለ ሰማያዊ ሕይወት አስረዳችው:: በስሟ የተቀረጸውን ጣዖትም ሰብራ አባቷን አስጠመቀችው:: እርሱም መንኖ ለዓመታት ኖረ:: ከዚያም ዻዻስ ሆኖ ተሹሟል::
+በዚህች ቀንም ስለ ክርስቶስ አንገቱን ተሰይፏል:: ቅድስት አውጋንያ ግን ከግብጽ ወደ ሮም ሒዳ የደናግል ገዳምን መሠረተች:: በሥሯም አምላክ 3,300 ደናግልን ሰበሰበላት:: እነርሱን ስታጽናና: ስትመክር: ስትመራ ለዓመታት ኑራ በአካባቢው ገዢ ሃይማኖቷን እንድትክድ ተጠየቀች::
+"እንቢ" በማለቷ እርሷም እንደ አባቷ በዚህች ቀን ተሰይፋ ሰማዕት ሆናለች:: አብረዋት የመነኑ 2ቱ ጃንደረቦችም ዻዻሳት ሆነው ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል::
<< *ድንግል: *መናኝ: *ፈዋሽ: *ናዛዥ: *አበ ምኔት: *እመ ምኔት: *ጻድቅትና *ሰማዕት ለሆነች ለእናታችን ቅድስት አውጋንያ ክብር ይገባል! >>
+"+ አባ ገብረ ናዝራዊ +"+
=>እኒህ ጻድቅ በ14ኛው መቶ ክ/ዘ የነበሩ ኢትዮዽያዊ ናቸው:: ጻድቁ ትግራይ (ገዳማቸው ያለበትና) ሽዋ አካባቢ በደንብ ይታወቃሉ:: የእርሳቸው የቆብ አባት የሆኑት አባ ጐርጐርዮስ የታላቁ አኖሬዎስ (የደብረ ጽጋጋው) ልጅ ናቸው::
+አባ ገብረ ናዝራዊ በምናኔ በየገዳማቱ ሲጋደሉ ከኖሩ በሁዋላ በምክረ አበው ራሳቸው ገዳምን መሥርተዋል:: ብዙ ደቀ መዛሙርትንም ሰብስበው ገዳሙ ታላቅ ሆኗል:: በወቅቱ ከገዳመ ዋሊ (ዋልድባ) ቀጥሎ ጥብቅ ሥርዓት የነበረበት ታላቅ ገዳምም ሆኖ ነበር::
+ለዚህም ምክንያቱ አባ ገብረ ናዝራዊ ፍጹም ተሐራሚ በመሆናቸው ማንኛውም መነኮስ ከአንድ ማዕድ ውጪ እንዲቀምስ የማይፈቅዱ ስለ ነበር ነው:: ከታላቁ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ቀጥሎም ሰንበትን አክብሮ በማስከበር ጻድቁ ትልቁን ቦታ ይይዛሉ::+በተለይ ቀዳሚት ሰንበት እንድትከበር ታግለዋል:: በበጐ አበ_ምኔትነታቸውም ብዙ ፍጹማንን ለሃገራችን አፍርተዋል:: ራሳቸው የበሰለ ነገር ወደ አፋቸው ሳያስገቡ 24 ሰዓት በዳዊት መዝሙር ይደሰቱ ነበር::
+ላባቸው እስኪንጠፈጠፍም ይሰግዱ ነበር:: ሐዋርያዊ ግብርን ለመፈጸምም ወንጌልን እየሰበኩ ያለቻቸውን ነገር ይመጸውቱ ነበር:: ዛሬ የጻድቁ ዕረፍታቸው ነው::
+"+ ቅዱስ ፊቅጦር ዘሻው +"+
=>ይህ ቅዱስ ከታላላቅ ሰማዕታት አንዱ ነው:: ሻው ማለት ሰማዕትነትን የተቀበለባት ቦታ ስትሆን "ፊቅጦር ካልዕም" ይባላል:: ከክርስቲያን ወላጆቹ የወረሰውን በጐነት አጽንቶ በቅን መንገድ ኑሯል::+ምንም ወጣት: የሃገር አስተዳዳሪ: ሃብታምና መልከ መልካም ቢሆንም ይህ ሁሉ ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየው አልቻለም:: (ሮሜ. 8:35) ዘመነ ሰማዕታት በደረሰ ጊዜም ክብሩን ንቆ: ስለ ክርስትና ብዙተ ሰቃይቶ: በዚህች ቀን ከነ ተከታዮቹ ሰማዕት ሆኗል:: ጌታም ቃል ኪዳንን ገብቶለታል::
=>አምላከ ቅዱሳን የወዳጆቹን ምሥጢረ ቅድስና አይሰውርብን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::
=>ታሕሳስ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=1.ቅድስት አውጋንያ ተጋዳሊት2.አባ ገብረ ናዝራዊ ንጹሕ3.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት4.ቅዱስ ፊልዾስ ሰማዕት5.ቅዱስ ናሆም ነቢይ
=>+"+ ነገር ግን ለበጐ ነገር ጥበበኞች: ለክፉትም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ:: የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል:: የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን:: +"+ (ሮሜ. 16:19)
✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞

Untitled

✝✝✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
✞✞✞ ታኅሣሥ 6 ✞✞✞
✞✞✞ እንኩዋን "ለድንግልና ሰማዕት ቅድስት አርሴማ" : "አባ አብርሃም" እና "ቅዱስ ስምዖን ጫማ ሰፊው" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
+*" ቅድስት አርሴማ ድንግል "*+
=>እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው:: መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው "በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና" (ማቴ. 5:11) የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል::
*ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት::*ቅድስት አርሴማ ይሕ ቀረሽ የማይሏት ውብ ናት::*ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት::*ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት::*ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት::
¤ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:
+አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ ጐርጐርዮስ የታላቁዋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-
1.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት2.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት3.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::
+ቅዱሱ 3ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::
+ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው:: በሁዋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኩዋ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::
+በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ:: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ::
+በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::
+ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::
+አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::
+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::
+የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ:: የንጉሡ እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን-ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም ቆፍረው አወጡት::
+ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው::ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::
+የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ኢትዮዽያ እንደ መጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል:: ለዚህም ይመስላል ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮዽያውያን ልዩ ፍቅር ያላት:: በዋናው ገዳሟ (ወሎ /ኩላማሶ/ : ስባ : ውስጥ የሚገኝ ነው) ጨምሮ ስሟ በተራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና::
+ነገር ግን ወንድሞቼና እሕቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ:: የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን:: አባ እንጦንስ እንዳሉት "በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና::" (መዝ. 75:5)
+በዚህ ዕለት ከሰማዕቷ ጋር የመንፈስ እናቷን ቅድስት አጋታን ልናስባት ይገባናል:: ይህች እናት እመ-ምኔት ስትሆን ቅድስት አርሴማን ታስተምራት: ታጸናት: ከጐኗም ትቆምላት ነበር:: ረሃቧን: ጥሟን: ስደቷን: መከራዋንም ሁሉ አብራት ተሳትፋለች:: በፍጻሜውም አብራት ተሰይፋለች::
+ይህች ዕለት ለቅድስት አርሴማና ለተከታዮቿ ሰማዕታት የፍሰትና የቅዳሴ ቤት መታሰቢያ ናት::
+"+ አባ አብርሃምና ቅዱስ ስምዖን ጫማ ሰፊው +"+
=>እነዚህ 2 ኮከቦች በ11ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ በምድረ ግብጽ ተነስተው ለቤተ ክርስቲያን ድንቅ ተአምርን የሠሩ አበው ናቸው:: እመ ብርሃን ማርያም ለሥራ እስክታገናኛቸው ድረስም እርስ በርስ አይተዋወቁም ነበር::
+"+ አባ አብርሃም +"+
=>ይህ ቅዱስ ትውልዱ ከሶርያ ሲሆን እጅግ የታወቀ ነጋዴ ነበር:: ከሶርያ ግብጽ እየተመላለሰ ሲነግድ ባለ ጸጋ ሆኖም ነበር:: ነገር ግን ክርስትናን አጥብቆ የተማረ: ነዳያንን የማይዘነጋ: ጾምና ጸሎትን የማይገፋና እኔን ብቻ ይድላኝ የሚል ሰው ስላልነበረ እግዚአብሔር ለታላቅ ሥራ ጠራው::
+የግብጽ 61ኛ ፓትርያርክ አባ ፊላታዎስ ባረፈ ጊዜ አበው ተተኪ ፍለጋ ሱባኤ ቢገቡ "ሶርያዊ አብርሃምን ሹሙ" አላቸው:: እርሱ "እንቢ" ቢልም አለቀቁትም:: እርሱም ከሆነስ ብሎ ሃብቱን እኩሉን ለነዳያን: እኩሉን ለገዳማት ሰጥቶ ባዶ እጁን ወደ መንበረ ዽዽስናው ወጥቷል:: በዘመነ ሲመቱም ልማደ ኃጢአትን ያርቅ ዘንድ ብዙ ተግቷል::
+"+ ቅዱስ ስምዖን ሰፋዪ +"+
=>በዚያው ዘመን በምስር (በአሁኗ CAIRO) አካባቢ ራሱን ደብቆ: ጫማ እየጠገነ: ነዳያንን እየመገበ: ድኩማንን እየረዳ: በፍጹም ትሕትና: በጾምና በጸሎት የኖረ አባት ነው:: አንዲት ወጣት ልታስተው ብትመጣም ስለ ክርስቶስ ትዕዛዝ አንድ ዐይኑን በመሳፈቻ አውጥቶ ጥሏል::
+"+ በእምነት ተራራ ሲነቀል +"+
=>በወቅቱ የነበረው የግብጽ ከሊፋ ፍልስፍና ወዳጅ በመሆኑ ምሁራንን ያከራክር ነበር:: አንድ አይሁዳዊ "ምሑር" ነኝ ባይም ከክርስቲያኖች ጋር መከራከር ፈልጐ ጠየቀ:: አባ አብርሃምና አባ ሳዊሮስ መጥተው ድል ነስተው: አሳፍረውት ሔዱ::
+እርሱም በቂም በማቴ. 17:20 ላይ ያለችውን ቃል ይዞ ሒዶ በከሊፋው ፊት አቀረበ:: ቃሉም:- "የሰናፍጭ ቅንጣት ታሕል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ ተነቀል . . . ብትሉት ይቻላቹሃል" ይላል::
+ከሊፋውም አባ አብርሃምን ጠርቶ "መጽሐፍ ቅዱሳችሁ እንደዚህ ይላል?" አለው:: "አዎ!" ሲል መለሰለት:: "አድርገህ አሳየኝ" ቢለው 3 ቀናትን ለምኖት ወጣ:: ሁሉም ክርስቲያኖች የ3 ቀን ምሕላ ሲይዙ አባ አብርሃም በእመቤታችን መቅደስ ለ3 ቀናት ያለ ምግብና እንቅልፍ አለቀሰ::
+እመ ብርሃን በሞገስ መጥታ "ጫማ ሰፊው ስምዖን ይህንን ያደርግልሃል" አለችው:: በምልክት ሒዶ: በፊቱ አዘንብሎ "አቤቱ ለገኖችህ ክርስቲያኖች ራራላቸው?" አለው::+ቅዱሱ ደንግጦ እንቢ እንዳይለው የድንግል ማርያምን ስም ጠራበት:: ቅዱስ ስምዖንም ለአባ አብርሃም "ሰው እንዳያውቀኝ አደራ!" ብሎት ወደ አንድ ግዙፍ ተራራ ሔዱ::
+ሕዝቡ ባንድ ወገን: ከሊፋውና ሠራዊቱ በሌላ ወገን ቆሙ:: ቅዱሳኑ ከምዕመናን ጋር "41 ኪርያላይሶን" አድርሰው: ሰግደው ቀና ሲሉ ተራራው ተነቅሎ በዓየር ላይ ተንሳፈፈ:: ለማጽናትም 3 ጊዜ ተነቅሎ ተተከለ::
+በሁዋላም ወደ ሌላ ቦታ አልፎ ተቀመጠ:: በዚህች ዕለትም በድንግል ምልጃ: በቅዱሳኑ ጸሎት ታላቅ ሞገስ ሆነ:: ወዲያው ግን ቅዱስ ስምዖን ተሰወረ:: ውዳሴ ከንቱን ይጠላልና:: አባ አብርሃምም በቀሪ ዘመኑ ተግቶ ዐርፏል:: ዛሬ የ2ቱም መታሰቢያ ነው::
+ሊቃውንትም ቅዱስ ስምዖንን ሲያደንቁ:-"ሰላም ለስምዖን በአፈ ማርያም ዘተአምረ::እንበይነ ትዕዛዙ ለወልዳ ከመ ዐይኖ አዖረ::ኢይሌብውዎ ሎቱ ወኢይጸግውዎ ክብረ::ሶበ ጸለየ ቀዊሞ ለሊቀ ዻዻሳት ድኅረ::ነቀለ ደብረ ወተከለ ደብረ" ብለዋል:: (አርኬ)
=>አምላከ ቅዱሳን ተራራ ያፈለሱበትን እምነታቸውን አይንሳን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
=>ታሕሳስ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=1.ቅድስት አርሴማ ድንግል2."119" ሰማዕታት (ማሕበሯ)3.ቅዱስ ስምዖን ጻድቅ (ጫማ ሠፊው)4.አባ አብርሃም ሶርያዊ5.ቅዱስ እንጣልዮስ ሰማዕት
=>+"+ እውነት እላቹሃለሁ:: የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል:: የሚሳናችሁም ነገር የለም:: +"+ (ማቴ. 17:20)
✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞

Untitled

<<✝✝ ታላቁ አባ ዳንኤል✝✝ >>   ታኅሳስ7
ይህ ቅዱስ አባት ስም አጠራሩ ክቡር ነው:: በሁሉ ነገሩ የተቀደሰ የገዳማውያን መብራትም ነው:: ከተረፈ ንጹሕ ሕይወቱ ጣዕመ መንግስተ ሰማያትን አይቷልና:: አባ ዳንኤል በትውልድ ግብጻዊ ሲሆን ዓለምን ንቆ (መንኖ) ገዳም የገባው ገና በወጣትነቱ ነው::ጊዜውም ዘመነ ጻድቃን (በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን) ነበር:: በገዳመ አስቄጥስና በደብረ ሲሐት ይታወቃል:: ታላቁዋ መካነ ቅዱሳን ገዳመ ሲሐት ዛሬም ድረስ በስሙ የምትጠራ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ እጅግ ለብዙ ዘመናት በውስጧ ተጋድሎ ፍሬ ስላፈራባት: ደቀ መዛሙርትን በቅድስና ስለ ወለደባት ነው::
ስለዚህም ዛሬም ድረስ "አባ ዳንኤል ዘደብረ ሲሐት" ተብሎ ሲጠራ ይኖራል:: ሌላኛው ስሙ ደግሞ "ዘገዳመ አስቄጥስ" ይሰኛል:: ገዳመ አስቄጥስ የታላቁ ቅዱስ መቃርስ ርስት ሲሆን በዓለም በስፋትም: ብዙ ቅዱሳንን በማፍራትም አንደኛ የሆነ ገዳም ነው::በዚህ ገዳም ላይ አበ ምኔት ሁነው የሚሾሙ አበው ሁሌም የብቃት መዓርግ ላይ የደረሱ ሲሆኑ ክብራቸው ከፓትርያርክ በላይ ነው:: አባ ዳንኤልም ከብዙ የቅድስና ዓመታት በሁዋላ በአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ሆኖ ተሹሞ እልፍ አእላፍ መነኮሳትን በጽድቅ መንገድ መርቷል::
ቅዱሱ ከትጋቱ የተነሳ ለምግብና ለእንቅልፍ ጊዜ አልነበረውም:: ቀን ቀን መነኮሳቱን ሲናዝዝ: ድውያንን ሲፈውስ: ሥርዓተ ገዳምን ሲቆጣጠር ይውላል:: ልክ ሲመሽ ጭው ወዳለውና ስውራን ወደ ሚገኙበት በርሃ ይወጣል::
በዚያም ሙሉውን ሌሊት የተሰወሩ አባቶችን ሲፈልግ ያድር ነበር:: በዚህም ምክንያት የብዙ ስውራንን ገድል የጻፈ ሲሆን ባረፉ ጊዜም ገንዞ በመቅበር በረከታቸውን ተሳትፏል:: ታላቅ ሙያንም ፈጽሟል::
እርሱ ገንዞ ቀብሮ: ዜናቸውን ከጻፈላቸው ሥውራን ቅዱሳንም እንደ አብነት እሥራኤላዊቷን ቅድስት ዓመተ ክርስቶስን (ለ38 ዓመት ራቁቷን በሥውር የኖረች) እና ቅድስት በጥሪቃ ንግሥትን (መንግስቷን ትታ በሥውር የኖረች ናት) መጥቀስ እንችላለን::
ከዚህ ባለፈም አባ ዳንኤል በሰው ዘንድ የተናቁትንም ማክበርን ያውቅበታል:: ለምሳሌ በሴቶች ገዳም "እብድ" ናት ተብላ በበር የተጣለችውን ቅድስት አናሲማን: በእስክንድርያ ከተማ ሊቀ ዻዻሳቱ ሳይቀር "እብድ" ነው ብለው የናቁትን ቅዱስ ምሕርካን: እብድ ሳይሆኑ ራሳቸውን የሠወሩ ቅዱሳን መሆናቸውን ገልጧል::
አባ ዳንኤል ሐዋርያዊም ነበር:: በጊዜው ጦማረ ልዮን የሚባል የኑፋቄ ደብዳቤ ይላክ ነበርና ለዚህ ኬልቄዶናዊ ኑፋቄ በትጋት ምላሽ ይሰጥ ነበር:: አንድ ቀንም በንጉሥ ትዕዛዝ ኑፋቄው በእርሱ ገዳም ሊነበብ ሲል ቅዱሱ ከወታደሩ ቀምቶ ስለ ቀደደው ለሞት እስኪደርስ ደብድበውታል::
ጻድቁ አባ ዳንኤል አንዴ አውሎጊስ የሚባል ደሃ ድንጋይ ጠርቦ እንግዳ ሲቀበል ተመልክቶ "ጌታ ሆይ! ይህንን ደግ ሰው ለምን ደሃ አደረከው?" ሲል በፈጣሪ ሥራ ገባ::ጌታም እንደ ወትሮው በገሃድ ተገልጦ "በነፍስህ ትዋሰዋለህ?" አለው:: "አዎ ጌታየ" ስላለው ጌታችን ለአውሎጊስ ሃብትን ሰጠው:: ግን ወዲያው የጦር አለቃና ጨካኝ ሰው ሆነ::ጻድቁ ወሬውን ሰምቶ ሊጠይቅ ቢሔድ የአውሎጊስ ወታደሮች ደበደቡት:: ጌታችንም አባ ዳንኤልን ወደ ፍርድ ዙፋኑ አቅርቦ "ወዳጄን መልስልኝ" አለው:: እመ ብርሃን ግን ቀርባ የልጇን እግር ሳመች::
"ልጄ ሆይ ማር!" አለችው:: ጌታም "እሺ" ብሎ ጻድቁን ወደ በአቱ: አውሎጊስን ወደ ቀደመ ግብሩ መለሳቸው:: የአባ ዳንኤል ድንቁ ብዙ ነው::
ሌላው ቢቀር ሽፍታ አባ ዳንኤልን መስሎ ወደ ደናግል ገዳም: ሊዘርፍ: በማታለል ገባ:: ደናግሉም ጻድቁ መስሏቸው እግሩን አጥበው ዐይነ ስውሯን ቢቀቧት ዐይኗ በርቷል:: ሽፍታውም ደንግጦ ንስሃ ገብቷል:: አባ ዳንኤል ግን ተጋድሎውን ፈጽሞ በዚህች ቀን ዐርፏል::

Untitled

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜንታኅሣሥ 8-መልአኩ የታዘዘውን ባለመፈጸሙ ኃይሉን አጥቶ በምድር ወድቆ ሳለ በጸሎታቸው አማልደው የቀደመ ክብሩን ያሰጡት ታላቁ አባት አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን ዕረፍታቸው ነው፡፡ + በሞት ማረፋቸውን መቋሚያቸው በሰው አንደበት ለመነኮሳቱ የተናገረችላቸው ኢትዮጵያዊው ጻድቅ የደብረ ድማው አቡነ ተክለ አልፋ ዕረፍታቸው ነው፡፡ + ቅዱሳት ደናግል ሴቶች በርባራና ዮልያና በሰማዕትነት ዐረፉ፡፡ + አባ ኤሲና እኅቱ ቅድስት ቴክላ በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡ + እመቤታችን ተገልጻለት የተቆረጠ እጁን እንደቀደሞው አድርጋ የፈወሰችው የሀገረ ደማስቆው አባ ዮሐንስ ዕረፍታቸው ነው፡፡ + አባ ያሮክላ ዕረፍቱ ነው፡፡+ አባ ገብረ ማርያም ዕረፍቱ ነው፡፡  + እንደነ ሄኖክና ኤልያስ በሞት ፈንታ የተሰወሩት አቡነ ሙሴ ልደታቸው ነው፡፡+ ታላቁ አባት አቡነ ኪሮስ ልደታቸው ነው፡፡ + ታላቁ አባት አቡነ እስትንፋስ ክርስቶስ ልደታቸው ነው፡፡      አባ ያሮክላ፡- የዚኽም ቅዱስ ወላጆቹ አስቀድሞ አረማውያን የነበሩ ናቸው፡፡ በኋላ ግን አምነው ተጠምቀው ልጃቸውም አባ ያሮክላ በእስክንድርያ አገር በቅዱስ ማርቆስ መንበር ከቅዱስ ዲሜጥሮስ ተካሌ ወይን ቀጥሎ 13ኛው ሊቀ ጳጳሳት እስከሚሆን ድረስ በጽድቅ የተመላለሰ ነው፡፡ ምእመናንንም በመልካም አጠባበቅ ጠበቃቸው፣ ብዙ አረማውያንንም ክርስቶስን ወደማመን መለሳቸው፡፡ ምእመናንንም በሃይማኖት በማጽናት መልካም አገልግሉቱን ፈጽሞ በሰላም ዐረፈ፡፡ + + + ሰማዕቱ አባ ገብረ ማርያም፡- ይኽም ቅዱስ የሰማዕታትንና የጻድቃንን በየዕረፍታቸው ቀን ለእያንዳንዳቸው የተራቡትን በማብላት የተራቆቱትን በማልበስ መታሰቢያቸውን የሚያደርግ ነው፡፡ እንዲህም ባለ ሥራ ሲኖር በዚያ ወቅት እስላሞች ወደ ሸዋ አገር መጡ፡፡ አባ ገብረ ማርያምም ያማሩ የክህነት ልብሶቹን ለብሶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ሲጸልይ እስላሞች ሰብረው ገብተው ራሱን በሰይፍ ቆረጡት፡፡ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀዳጀ፡፡ + + + በሞት ፈንታ የተሰወሩት አቡነ ሙሴ ልደታቸው ነው፡፡ እኚህም አቡነ ሙሴ በግብፅ 40 ዘመን ነግው ሳለ ንግሥናቸውን ትተው ወደ ኢትዮጵያ መተው በምነና ሕይወት እየኖሩ 16 ፍልፍል ቤተመቅደሶችን የሠሩ ሲሆን 8ቱ የተሰወሩ ናቸው፡፡ በገዳማቸው በቅድስቱ ውስጥ ጥልቀቱ የማይታወቅ እጅግ ጥልቅ የሆነ ጉድጓድ አለ፡፡ በውስጡም ስውራኑ አብያተ ክርስቲያናት ይገኙበታል፡፡ እናታቸው ጵርስቅላ ጌታችን በሠርግ ቤት ተገኝቶ ውኃውን ወደ ወይን የለወጠለት የዶኪማስ ልጅ ናት፡፡ ጌታችን በስብከቱ ‹‹ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልሏቸው›› ብሎ ካቀፋቸውና ካስተማረባቸው ሕፃናት አንዱ ይኽ አቡነ ሙሴ ናቸው፡፡ ጻድቁ በግብፅ ነግሠው 40 ዓመት በንግሥና ገዝተዋል፡፡ ከጨለማ ወደ ብርሃን ያመጡን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሲያርፉ በቅዱስ አትናቴዎስ ተሹመው 2ኛው የኢትዮጵያ ጳጳስ ሆነው መጡ፡፡ ሲሾሙም ሚካኤል ወገብርኤል በወርቅ ወንበር አስቀምጠው ‹‹ይገባዋል ይገባዋል›› ብለው ቅብአ ክህነት ቀብተዋቸዋል (ጵጵስና ሾመዋቸዋል፡፡) ጻድቁ እንደ አቡነ ዘርዐ ቡሩክ 12 ክንፍ የተሰጣቸው ናቸው፡፡ (የዕረፍታቸውን ዕለት መስከረም አራትን ይመለከቷል)      + + + አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን፡- የትውልድ ሀገራቸው ደቡባዊ ግብፅ ሲሆን በ14 ዓመታቸው ነው አስቄጥስ ገዳም ገብተው የመነኮሱት፡፡ በመነኮሱበት ዕለትም መልአክ ከጎናቸው ቆሞ ታይቷል፡፡ ታላቁ አባት አባ አጋቶን ካረፉ በኋላ ገዳመ አስቄጥስን ያስተዳደሩት አቡነ ሳሙኤል ናቸው፡፡ በዓለም ታሪክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት በተከፈለችበትና ‹‹የውሾች ጉባኤ›› በተባለው በ451 ዓ.ም በተካሄደው ጉባኤ ላይ የእነ ልዮን የክህደት ቃለ ጉባኤ ለአቡነ ሳሙኤል ተልኮላቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ቃለ ጉባኤውን ተቀብለው መነኮሳቱን ሰብስበው እያሳዩአቸው በእሳት አቃጥለውታል፡፡ በዚህም ጊዜ በገዳሙ ለ14 ቀን ያህል ቀስተ ደመናና ብርሃን ወርዶ ታይቷል፡፡ ልዮንም ይህንን ሲሰማ ለንጉሡ በመንገር አቡነ ሳሙኤልን ሊያስገድላቸው ሲል እመቤታችን ለአቡነ ሳሙኤል ተልጻላቸው ወደ ደብረ ቀልሞን እንዲሄዱ ነገረቻቸው፡፡ እሳቸውም ተነስተው ደብረ ቀልሞን ገቡ፡፡ በገዳሙ በአበምኔትነት ተሹመው ማገልገል ጀመሩ፡፡ አቡነ ሳሙኤል በዚሁ ዘደብረ ቀልሞን ገዳም የእግዚአብሔርን መልአክ አማልደው መልአኩን ምሕረት ያሰጡ ታላቅ አባት ናቸው፡፡ መልአኩ የታዘዘውን ባለመፈጸሙ ኃይሉን አጥቶ በምድር ወድቆ ቀርቶ ነበር፡፡ ሁለት ልጆች በገዳሙ ውስጥ ሆነው በቅዳሴ ጊዜ ሲሮጡና ሲዘፍኑ መልአኩ ሁለቱንም ልጆች በሞት እንዲቀስፋቸው ተላከ፡፡ ከልጆቹም አንደኛው መልኩ እጅግ የተዋበ ድምፁም ያማረ ስለነበር መልአኩ አሳዝኖት ‹‹አንተንስ የፈጠረህ ይቅሰፍህ?›› ብሎ ተወውና በማዳላት ሌላኛውን መልኩም ድምፁም የማያምረውን ልጅ ብቻ ቀስፎ ሊያርግ ሲል ኃይሉን ተነጥቆ በመሬት ላይ ወደቆ ቀረ፡፡ ሄዶም ከቤተልሔሙ በራፍ ላይ ወደቀ፡፡ በቀጣዩ ቀን ዲያቆኑ ለተልእኮ ሲሄድ እዚያ ወድቆ ቢያየው እጅግ ደንግጦ ‹‹ሰማያዊ ነህ ወይስ ምድራዊ? ከዚህስ ምን ትሠራለህ?›› አለው፡፡ መልአኩም ‹‹በአፈጣጠሬስ ሰማያዊ ነበርኩ ነገር ግን ምግባሬ ምድራዊ አድርጎኛል›› አለው፡፡ መልአኩም በመቀጠል ‹‹እባክህ ሄደህ አባ ሳሙኤልን ከበዓቱ ጥራልኝ›› አለው፡፡ ዲያቆኑም አቡነ ሳሙኤልን ጠርቶለት አቡነ ሳሙኤል መጡና በሐዘን ውስጥ ሆነው ‹‹ምን እንዳደርግልህ ትወዳለህ?›› አሉት፡፡ መልአኩም ‹‹አማልደኝ›› አላቸው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም በእመቤታችን ሥዕል ሥር ሄደው እመቤታችንን እያለቀሱ በመጸለይ ተማጸኗት፡፡ እመቤታችንም ተገለጠችላቸውና ‹‹ሕዝቡን ሁሉ ሰብስበህ 41 እግዚኦታና 41 በእንተ ማርያም አድርሰህ ክንፍና ክንፉን ይዘህ ተንስዕ በስሙ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወበስማ ለእግዝእትነ ማርያም ብለህ አንሳው›› አለቻችው፡፡ አቡነ ሳሙኤልም እመቤታችን እንደነገረቻቸው አደረጉለትና መልአኩ ኃይሉ ተመለሰለት፡፡ ወዲያውም በማዳላት ሳይቀስፈው የቀረውን ልጅ ቀስፎ ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡ ያም መልአክ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከደብረ ቀልሞን ገዳም በረድኤት ተለይቶ አያውቅም፡፡ ቃልኪዳንም ስለተቀበለበት በገዳሙ ውስጥ ርሀብ፣ ቸነፈርና መቅሰፍት ፈጽሞ አይገባም፡፡ ‹‹መምሕረ ንስሓ-the confessor›› በመባል የሚታወቁት አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን ወንጌልን በማስተማር፣ አስደናቂ ተአምራትን በማድረግ ድውያንን እየፈወሱ በብዙ ድካም ከተጋደሉ በኋላ ከጌታችን ቃልኪዳን ተቀብለው ታኅሣሥ 8 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፈዋል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንኳን የሰውን ልጅ ይቅርና ጸጋቸውን የተገፈፉ መላእክትንም ጭምር ማማለድ የሚችሉ አባቶችና እናቶች ያሏት ናት፡፡ + + + ቅድስት በርባራና ቅድስት ዮልያና፡- ይህችም ቅድስት በርባራ በከሃዲው መክስምያኖስ ዘመነ መንግሥት በቤተ መንግሥት ውስጥ ታላቅ መስፍን ለሆነው ለዲዮስቆሮስ ልጁ ናት፡፡ እርሱም ሴት ልጁን ማንም እንዳያይበት ታላቅ የሆነ ሕንፃን አሠራ፡፡ መታጠቢያ የውሽባ ቤት በግንብ ሠራና የሚከፈቱ ሁለት መስኮቶችንም በውስጡ እንዲኖሩ አደረገ፡፡ ቅድስት በርባራም ሁለቱን መስኮቶች ባየች ጊዜ ሦስተኛ መስኮትን እንዲሠሩ አናፂዎቹን አዘዘቻው፡፡ ከዚህም በኋላ አዳኝ በሆነ በጌታችን ቅዱስ መስቀል አምሳያ በውኃ መታጠቢያው ላይ አሠራች፡፡አረማዊ የሆነው መስፍኑ አባቷም ወደሕንፃው በገባ ጊዜ ልጁ ያሠራችውን አይቶ አናፂዎቹን ጠርቶ ‹‹ይህ ምንድነው?›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ይህን እንድንሠራ ያዘዘችን ልጅህ ናት›› አሉት፡፡ አባቷም ቅድስት በርባራን ጠርቶ ‹‹ለምን እንዲህ አደረግሽ?›› አላት፡፡ እርሷም ‹‹አባቴ ሆይ! አስተውል ልዩ ሦስት በሆነ በሥላሴ ስም ሥራ ሁሉ ይፈጸማልና ስለዚህ ሦስተኛ መስኮት አሠራሁ፡፡ ይህም መስቀል አለሙ ሁሉ በእርሱ በዳነበት በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል አምሳል ነው፣ አንተም አባቴ ሆይ ከስሕተትህ ተመልሰህ የፈጠረህን አምልከው›› አለችው፡፡ይህንንም ቃል አባቷ ከቅድስት በርባራ በሰማ ጊዜ እጅግ ተናዶና ተቆጥቶ ሰይፉን መዝዞ በኋላዋ ሮጠ፡፡ እርሷም አጥብቃ በሸሸች ጊዜ በፊቷ ያለች ዓለት ተሰንጥቃ በውስጧ ሠወረቻትና ለአባቷ ሰይፍ አዳነቻት፡፡ በሌላም ጊዜ ቅድስት በርባራ ወደ አባቷ ተመልሳ መስክርነቷን ቀጠለች፡፡ አባቷም ካሠቃያት በኋላ ዳግመኛ ለሌላ መኮንን እንዲያሠቃያት አሳልፎ ሰጣት፡፡ ያም መኮንን ጽኑ በሆነ ሥቃይ አሠቃያት፡፡ በዚያም ዮልያና የምትባል ሴት ነበረችና ቅድስት በርባራን በሥቀይ ውስጥ ሆና ባየቻት ጊዜ ሄዳ አጽናናቻት፣ አረጋጋቻት፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችንም ለቅድስት በርባራ ተገለጠላትና አረጋግቶ ተስፋውን ሰጣት፡፡ከዚህም በኋላ የቅድስት በርባራ በእምነቷ መጽናቷን ባየጊዜ ወላጅ አባቷ አንገቷን በሰይፍ እንዲቆርጡት አዘዘ፡፡ እንዳዘዘውም ቅድስት በርባራን ከባልንጀራዋ ከቅድስት ዮልያና ጋር አንገታቸውን በሰይፍ ቆረጧቸውና የሰማዕትነት ፍጻሜያቸው ሆኖ የክብር አክሊልን ተቀዳጁ፡፡ ወዲያውም እሳት ከሰማይ ወርዶ አባቷንና ጓደኛው የሆነ መኮንኑን መርትያኖስን አቃጠላቸው፡፡ ቅድስት በርባራ በውሽባ ቤት በመስቀል ምልክት ያሠራችው ያም መታጠቢያ ቤት ለታመመ ሁሉ ከእርሱ በታጠበ ጊዜ የሚያድን በውስጡ ታላቅ ፈውስ ያለበት ሆነ፡፡ ከዚህም በኋላ የቅዱሳት ደናግል ሰማዕታቱን ሥጋቸውን ወስደው ከከተማው ውጭ ባለች ቤተ ክርስቲያን ስሟ ገላልያ በሚባል ቦታ አኖሯቸው፡፡ ቅዱስ ሥጋቸውም በቅዱሳን ሰማዕታት በአቡ ቂርና በዮሐንስ በምስር አገር ባለች ቤተ ክርስቲያናቸው እስከዛሬ ድረስ አለ፡፡ + + +            አቡነ ተክለ አልፋ ዘደብረ ድማህ፡- ኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ አልፋ ልደታቸውም ዕረፍታቸውም ታኅሣሥ 8 ነው፡፡ ‹‹ተክለ አልፋ›› ማለት ለዘለዓለም የሚኖር ድንቅ ሥራ ማለት ነው፡፡ ጻድቁ ቀደምትና ዓበይት ከተባሉት ከ72 ቅዱሳን ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡ በደብረ ድማህ አበምኔትነት ተመርጠው ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡ የሴቶችን ማኅፀን የምታበላሸውንና መካን የምታደርገውን ‹‹እመ ሙላድ›› የተባለችውን ዛር አቡነ ተክለ አልፋ በመቋሚያቸው እንደ አውሬ አባረው አጥፍተዋታል፡፡ እርሷም እንደ ሰው ትልካ ሄዳ ማኅፀን የምታጠፋ ነበረች፡፡ ከዚህም በኋላ አቡነ ተክለ አልፋ ሹመትን አልፈልግም ብለው በጸሎት ብቻ ተወስነው የኖሩ በዲማ ትልቅ ክብር ታላቅ አባት ናቸው፡፡ በተወለዱበት ዕለት ታኅሣሥ 8 ቀን ሲያርፉ ማረፋቸውን መቁዋሚያቸው ናት በሰው አንደበት ‹‹አባታችን ዐረፉ›› ብላ ለመነኮሳቱ የተናገረችው፡፡ ጻድቁ የጠቀበሩት በተሾሙበትና ለ35 ዓመታት ባገለገሉበት በዚያው በዲማህ ነው፡፡ + + +            አባ ኤሲና እኅቱ ቅድስት ቴክላ፡- እነዚህም ቅዱሳን ለእስሙናይን በስተምራብ ካለው አውራጃ ብጺር ከሚባል መንደር የተገኙ ሰማዕታት ናቸው፡፡ አባታቸው ኤልያስ እናታቸው ማርያም ይባላሉ፡፡ ኤሲም ዕድሜው እንደደረሰ ወላጆቹ ሊያጋቡት ሲሉ እርሱ ግን እምቢ አለ፡፡ ኤሲ እግዚአብሔርን እጅግ የሚፈራ ብዙ ሀብት የነበረው እጅግ ባለጸጋም ነበር፡፡ እጅግ የበዙ በጎች ስለነበሩት ጸጉራቸውን እየሸጠ ድኆችንና ጦም አዳሪዎችን ይረዳል፡፡ ዕድሜውም 20 በሆነ ጊዜ አባቱና እናቱ ሞቱ፡፡ ከሃዲው ንጉሥ አረመኔው ዲዮቅልጥያኖስም በዚያ ዘመን ነግሦ የክርስቲያኖችን ደም እንደ ውኃ ማፍሰስ ጀመረ፡፡ አባ ኤሲም በእስክንድርያ አገር ጳውሎስ ከሚባለው ባልንጀራው ጋር የታሰሩትን ሰማዕታት እየጎበኟቸው ያገለግሏቸው ነበር፡፡ ሰማዕታቱም ለአባ ኤሲና ለጳውሎስ ‹‹እናንተም እንጂ ደግሞ ሰማዕት ትሆኑ ዘንድ አላችሁ›› እያሉ ትንቢት ይነግሯቸው ነበር፡፡ በዚያም ወራት የንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ባለሟል የነበረውን የኅርማኖስን ልጅ ታላቁን ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦርን ወደ እስክንድርያ በግዞት እያሠቀዩ አመጡት፡፡ ኤሲና ጳውሎስም የቅዱስ ፊቅጦርን ጽናት አይተው መንፈሳዊ ቅናት ቀኑ፡፡ ኤሲም ወደ መኮንኑ ቀርቦ የጌታችንን ክብር መሰከረ፡፡ መኮንኑም ኤሲን ይዞ ማሠቃየት ጀመረ፡፡ከዚህም በኋላ ኤሲን በብረት አለንጋ ብዙ ግርፋትን ገረፉት፡፡ ህዋሳቱንም በሾተሎች ሰነጣጠቁ፡፡ በሥጋውም የችቦ መብራቶችን እያደረጉ አቃጠሉት፡፡ ዳግመኛም በሰንሰለት አሥረው በሚነድ እቶን እሳት ውስጥ ጨመሩት፡፡ ነገር ግን ወደ ጌታችን በጸለየ ጊዜ ጌታችን መልአኩን ቅዱስ ሱርያልን ላከለት፡፡ መልአኩም ለኤሲ ‹‹ጻድቅ ሰው ሆይ ሰላምታ ለአንተ ይገባሃል›› አለውና እሳቱን አጠፋለት፡፡ እጁንም ይዞ ከጉደጓዱ አወጣው፡፡ አባ ኤሲም ወደ መኮንኑ ዘንድ ሄዶ ‹‹ከሃዲ ንጉሥ ሆይ አንተ ጣዖታቶችህ እፈሩ አምላኬ አድኖኛል›› አለው፡፡ ሕዝቡም አባ ኤሲን ሕያው ሆኖ ባዩት ጊዜ እጅግ ተደንቀው ‹‹እኛም በአባ ኤሲ አምላክ አምነናል›› ብለው መስክረው ብዙዎች ሰማዕት ሆኑ፡፡ አባ ኤሲንም አሠሩት፡፡ ከዚህም በኋላ ለእኅቱ ለቅድስት ቴክላ የታዘዘ መልአክ ተገለጠላትና ወደ ወንድሟ እንድትሄድ ነገራት፡፡ እርሷም ከእንዴና ከተማ ተነሥታ ወደ ባሕር ዳርቻ በደረሰች ጊዜ መንፈሳዊት መርከብን አገኘች፡፡ እመቤታችንና አክስቷ አልሳቤጥም በውስጧ አሉ፡፡ ቅድስት ቴክላም ‹‹እመቤቶቼ ሆይ! የደረሰባችሁ ምንድነው/አዝናችሁ አያችኋለሁና›› አለቻቸው፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹በእርጅናዬ ወራት የወለድኩት አንድ ልጅ ነበረኝ፣ ወስደው አረዱብኝ›› አለቻት፡፡ እመቤታችን ድንግል ማርያምም ‹‹ለእኔም አንድ ልጅ ነበረኝ፣ እርሱንም ወስደው ሰቅለው ገደሉብኝ›› አላቻት፡፡ ቅድስት ቴክላም ይህንን በሰማች ጊዜ እጅግ አዝና ‹‹እመቤቶቹ ሆይ! በእውነት ጽኑ የሆነ ሀዘን አግኝቷችኋል›› አለቻቸው፡፡ ይህንና የመሳሰለውንም ነገር እየተነጋገሩ ወንድሟ አባ ኤሲ ካለበት አደረሷት፡፡ የተገለጡላት ግን እነማን እንደሆኑ አላወቀችም፡፡ አባ ኤሲም እኅቱን ቴክላን ባያት ጊዜ ደስ አለው፡፡ አብረው ስለጌታችን ክብር ይሞቱ ዘንድ ተስማሙ፡፡ ሌሊት በሆንም ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ሱርያል አባ ኤሲን ነጥቶ ወደ ሰማይ ወሰደውና ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን አሳየው፡፡ የጻድቃንንና የሰማዕታትን መኖሪያቸውን የራሱንም መኖሪያውን አሳየው፡፡ መልአኩ ‹‹በሰማዕታት ስም የሚዘክሩ የዓለም ሰዎች ቢኖሩ በዕለተ ሞታቸው ቀን የዘከሯቸው ቅዱሳን አማልደው በዚህ የብርሃን ድንኳን አዳራሽ ውስጥ ለዘለዓለም በክብር ያኖሯቸዋል›› እያለ እያንዳንዱን የቅዱሳንን የብርሃን ድንኳን ያለውን የቅዱሳንን መኖሪያ አሳየው፡፡ ከዚህም በኋላ ቅዱሳን ሁሉ መጥተው አባ ኤሲን ሰላምታ ሰጡት፡፡     መልአኩም አባ ኤሲን ሰማዕትነቱን እንዲፈጽም ከነገረው በኋላ ከሰማያዊት ኢየሩሳሌም መልሶ አምጥቶ እሥር ቤቱ ውስጥ አስቀመጠውና ተመልሶ ዐረገ፡፡ በነጋም ጊዜ መኮንኑ አባ ኤሲንና እኅቱን ቅድስት ቴክላን ከእሥር ቤት አውጥተው ጽኑ በሆኑ ልዩ ልዩ ሥቃዮች አሠቃዩአቸው፡፡ በተሸከርካሪዎች መሣሪያ፣ በብረት ቃጠሎ፣ በችንካሮች በመቸንከር የራሳቸውንም ቆዳ በመግፈፍ ብዙ አሠቃዩአቸው፡፡ ነገር ግን ጌታችን ከሕመማቸው ሁሉ ፈወሳቸው፡፡ መኮንኑም ማሠቃየት በሰለቸው ጊዜ ወደላይኛው ግብጽ ይወስዳቸውና ያሠቃያቸው ዘንድ ለእንዴናው አገር መኮንን አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ 8 ቀን ያህል እንደተጓዙም መርከቧ ቆመች፡፡ ከዚህም በኋላ መኮንኑ የአባ ኤሲንና የቅድስት ቴክላን ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ አዘዘ፡፡ እነርሱም በዚህ ደስ ተሰኝተው ጸሎታቸውን ከፈጸሙ በኋላ አንገታቸውን አሳልፈው ለሰያፊዎቻቸው ሰጧቸውና በየተራ ቆረጧቸው፡፡ ሰማዕትነታቸውንም በዚሁ ፈጽመው የክብርን አክሊል ተቀዳጁ፡፡ እግዚአብሔርም ስንሑፍ ከሚባል አገር ስሙ ኦሪ የሚባለውን ቄስ የቅዱሳንን ሥጋቸውን እንዲያነሣ አዘዘው፡፡ እርሱም መጥቶ በክብር ወስዶ የመከራው ዘመን እስኪያልፍ በንጹሕ ቦታ አኖራቸው፡፡ ከሥጋቸውም ብዙ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራት ተፈጽመው ታዩ፡፡ ከእነርሱም ጋር አብረው ተሰይፈው የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበሉ ቅዱሳን 477 ናቸው፡፡ + + + አባ ዮሐንስ ዘሀገረ ደማስቆ፡- ይኽም ቅዱስ ከደማስቆ ከከበርቴዎቿና ከታላላቆቿ ወገን ከሆነው መንሱር ከሚባለው ሰው የተወለደ በጥበብና በፈሪሃ እግዚአብሔር ያደገ ነው፡፡ የቀርሊ ፈላስፋ ከሆነው ቁልፋህ ከሚባል መነኩሴ ቁልዝማቂ መምህሩ ዘንድ የፍልስፍና ትምህርትን ተማረ፡፡ ትምህርቱንም ሲጨርስ ቁልዝማዊ መምህሩን ተሰናብቶ ወደ ከበረ ሊቅ ሳበ ሰማዕት ገዳም ሄደ፡፡ አባቱም በሞተ ጊዜ ለአገረ ገዥው ጸሐፊ ሆነ፡፡በዚያም ወራት የከሃዲው ልዩን ልጅ ቆስጠንጢኖስ ተነሥቶ በአምላክ ፈቃድ ስለተሣሉ ቅዱሳት ሥዕላት ጸብ በማንሣት አብያተ ክርስቲያናትን የሚያውክ ሆነ፡፡ ይህም አባ ዮሐንስ የቤተ ክርስቲያን ሹመት ሳይኖረው በቀናች ሃይማኖት እያጸናቸው በአምላክ ፈቃድ ለተሣሉ ሥዕላት ስግደት እንደሚገባ ምስክር ከቅዱሳት መጻሕፍት እያመጣ የሚጽፍ ሆነና ወደ ምእመናን ሁሉ የሚልክ ሆነ፡፡ ከሃዲው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስም ይህንን በሰማ ጊዜ ጥርሱን እያፋጨ በዮሐንስ ብዕር አምሳል የሚጽፍ ጸሐፊ ፈልጎ አመጣና ዮሐንስ እንደጻፈው አድርጎ እንዲህ ብሎ ጻፈ፡- ‹‹ከአንተ ዘንድ ያለው ዮሐንስ ከአንተ ጋር ተዋግቼ አገርህን እማርክ ዘንድ ይህን ደብዳቤ ጽፎ ላከልኝ›› ብሎ በወንጀል ለደማስቆው ገዥ ላከለት፡፡ የደማስቆውም ገዥ የተጻፈለት እውነት መስሎት የቅዱስ ዮሐንስ ቀኝ እጁን ቆረጠው፡፡ አባ ዮሐንስም የተቆረጠች እጅን ይዞ ወደ የብርሃን እናቱ ወደሆነች ወደ እመቤታችን ሥዕል ሄዶ በብዙ ዕንባ እንዲህ ብሎ ለመናት፡- ‹‹እመቤቴ ሆይ! ለሥዕልሽ መስገድ እንደሚገባ በተጣላሁ ጊዜ ነው ይህ የእጄ መቆረጥ የደረሰብኝ፣ አሁንም ሁሉ ይቻልሻልና በቸርነትሽ ፈውሽኝ›› ብሎ ከለመናት በኋላ ወዲያው ከባድ እንቅልፍ ጣለው፡፡ በእንቅልፉም ሳለ እመቤታችን ተገለጸችለትና እጁን እንደቀደሞው አድርጋ መለሰችለት፡፡ እርሱም በነቃ ጊዜ እጁ ድና ስላገኛት እጅግ ተደስቶ እመቤታችንን አመሰገናት፡፡ከዚህ በኋላ ወደ ገዳም ሄዶ መነኮሰ፡፡ መምህሩ የሆኑት አንድ አረጋዊ አባትም ‹‹ዮሐንስ ሆይ አፍአዊት ከሆነች ትምህርትህ ምንም ምን አታድርግ ግን ዝምታን ተማር›› አሉት፡፡ ዮሐንስም የመነኮሳቱን የመጸዳጃ ቤታቸውን እያጸዳና በሁሉ ነገር እያገለገላቸው በተጋድሎ ኖረ፡፡ መምህሩም አርምሞውን ፈትቶ ካገኙት ይቀጡት ነበር፡፡ እመቤታችንም አንድ ቀን ለመምህሩ ተገለጠችላቸውና ዮሐንስ ድርሳናትን እንዲደርስ ይፈቅድለት ዘንድ አዘዘችው፡፡ ዮሐንስም ከዚህ በኋላ ብዙ ድርሳናትን ደረሰ፡፡ ስለ ቀናች አንዲት ሃይማኖትና ስለተሣሉ ቅዱሳት ሥዕላት ብዙ የደከመው አባት አባ ዮሐንስ የእርጅና ዘመኑን ጨርሶ በዚህች ዕለት በሰላም ዐረፏል፡፡ + + + ዳግመኛም በዚህች ዕለት ታላላቆቹ ቅዱሳን አባቶቻችን አቡነ ኪሮስና አቡነ እስትንፋስ ክርስቶስ ልደታቸው ነው፡፡ ረድኤት በረከታቸውን ይክፈለን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

Untitled

✝✞✝ ታኅሣሥ 9 ✝✞✝
✝✞✝ እንኩዋን ለጻድቅና ሰማዕት "ቅዱስ በአሚን" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝
+*" ቅዱስ አባ በአሚን "*+
=>የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም:: ይልቁኑ:-¤እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው::¤እንደ ብዕር አጥንታቸው::¤እንደ ብራና ቆዳቸው ሆኖ ተጽፏል እንጂ:: ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው::
+ስለዚህም "ተጋዳዮች : የሚያበሩ ኮከቦች : የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች" ተብለዋል:: እነሱ እየቀለጡ አብርተዋልና::
+ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም "ዘመነ ሰማዕታት" የሚባለው ከ150 እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያለው ዘመን ነው::
+በተለይ ግን ከ270ዎቹ እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና የክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል:: የሰማዕታት ምሥጢራቸው ቃለ ወንጌል: የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም:: (ማቴ. 10:16, ማር. 13:9, ሉቃ. 12:4, ዮሐ. 16:1, ሮሜ. 8:35, ራዕይ. 2:9)
+የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ዻዻሳት ነው::
=>ከዓበይት ሰማዕታትም አንዱ ቅዱስ በአሚን ነው:: በቤተ ክርስቲያን "ሰማዕት ዘእንበለ ደም (ሰይፍ)" የሚባሉ ቅዱሳን አሉ:: ሰማዕት ዘእንበለ ደም ማለት "እንደ ሰማዕታት መከራውን ሁሉ ተቀብለው ሳይሰየፉ (ሳይገደሉ) የመከራውን ዘመን ያለፉ" ናቸው::
+ለምሳሌ ከሠለስቱ ምዕት (ከ318ቱ ሊቃውንት) አብዛኞቹ እንደዚህ ባለ ሕይወት ያለፉ ናቸው:: ቅዱስ በአሚንም እንዲሁ ዓይነት ዜና ሕይወት ያለው አባት ነው::
¤ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
+ቅዱስ በአሚን ተወልዶ ያደገው በደቡብ ግብጽ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ቅዱሱ ከልጅነቱ ክርስትናን የተማረ ነበርና ሰው ሁሉ የሚወደው ታማኝ ሰው ሆነ:: ምንም ሃብታም ሰው ባይሆንም ተቀጥሮ ሠርቶ በሚያገኛት ገቢው መልካምን ይሠራ ነበር::
+በዘመኑም ከቅንነቱ የተነሳ "መታመንስ እንደ በአሚን" ይባል ነበር:: ቅንነቱን የወደዱ ሁሉ ይሹት ነበር:: በከተማው ውስጥ እጅግ ብዙ ሃብት የነበራቸው ባል እና ሚስትም ወደ ቤታቸው ወስደው መጋቢ (ተቆጣጣሪ) አደረጉት::
+ጠባዩን ከተረዱ በሁዋላ ግን ሙሉ ሃብት ንብረታቸውን በእጁ አስረክበውት ያስተዳድርላቸው ነበር:: ሲወጡና ሲገቡም እያዩት ደስ ይሰኙበት ነበር:: እርሱ ግን ልቡ በክርስቶስ ፍቅር የተመሰጠ ነበርና ለዚህ ዓለም ጉዋዝ ትኩረትን አይሰጥም ነበር:: ይጾም ይጸልይ ነበር እንጂ::
+አንድ ቀን ግን የቤቱ ባለቤቶች (ባልና ሚስት) ሲመጡ ቤታቸው እንደሚገባ ተደራጅቶ: ቁልፉ ተቀምጦ አገኙት:: ወዳጃቸው በአሚን ግን የለም:: ደንግጠው ቢያፈላልጉት ሊያገኙት አልቻሉም:: በመጨረሻ ግን መንኖ ገዳም መግባቱን ሰምተው ፈጽመው አዘኑ::
+ከእርሱ መለየትን አይፈልጉም ነበርና:: አልቅሰው ወደ ቤታቸው ሊመለሱ ሲሉ ሚስት "አይሆንም! ሔደን እናምጣው" ስላለች ወደ መነነበት ገዳም ሔደው: እያለቀሱ ይመለስላቸው ዘንድ ለመኑት::
+እርሱ ግን "ለሰማያዊ ሠርግ ታጭቻለሁና ከእንግዲህ የክርስቶስ ነኝ" አላቸው:: እንዳልተሳካላቸው ሲያውቁ ፈጽመው እያዘኑ ወደ ቤታቸው ተመለሱ:: ቅዱስ በአሚን ግን ገዳማዊ ሕይወትን በተጋድሎ ጀመረ::
+ይጾማል: ይጸልያል: ይሰግዳል: ይታዘዛል:: በዚህ መንገድ ሥርዓተ ገዳምን በበርሃ ሆኖ ሲፈጽም በዓለም እነ ዲዮቅልጢያኖስ ክርስቲያኖችን ይገድሉ ነበር::
ዜና ሰማዕታትም ቀስ እያለ ቅዱሱ ወዳለበት ገዳም ደረሰ::
+ነገሩን ሲሰማ ደስ አለው:: እርሱ ስለ ክርስቶስ ሲሉ ደምን ማፍሰስና መከራን መቀበል ከሁሉም ነገር የተሻለ እንደ ሆነ ያውቅ ነበርና:: ቀጥሎም ወደ ከተማ ሒዶ ደሙን ለማፍሰስ በቁርጥ ወስኖ ዘለቀ::
+በዚያም የንጉሥ ወታደሮች አግኝተውት ለጣዖት ይሰዋ ዘንድ ታዘዘ:: ቅዱስ በአሚን ግን "መስዋዕት የሚገባው ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ: ለባሕርይ አባቱ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ነው:: ለፍጡር አልሰዋም" ሲል መለሰላቸው:: በዚህም ምክንያት ወታደሮች እየተፈራረቁ ደበደቡት::
+ደሙንም አፈሰሱት:: ምንም እንዳልተለወጠ ሲያውቁ ወደ እስር ቤት ጨመሩት:: ከዚያም በቀን በቀን እያወጡ ይደበድቡት: በእሳት ያቃጥሉት: በተለያዩ ማሰቃያዎች በመከራ ያውሉት ነበር:: እርሱ ግን ክርስቶስን ከመቀደስ በቀር አንዳች አይመልስላቸውም ነበር::
+በብዙ አሰቃይተው እንቢ ቢላቸው ወስደው በጨለማ ቤት ዘጉበት:: በዚያም ጥለውት ዓመታት አለፉ:: ሁሉንም በጊዜው የሚሠራ ጌታ ግን እነዚያን የመከራ ዘመናት አሳልፎ ዲዮቅልጢያኖስና መክስምያኖስን አጠፋቸው::
+በፈንታቸውም መፍቀሬ ክርስቶሳውያን ቅዱስ ቆስጠንጢኖስን አነገሠ:: አብያተ ክርስቲያናት ታነጸ:: ስለ ክርስቶስ የታሠሩ ሁሉ ነጻ ወጡ:: በዚህ ጊዜ ምዕመናን መጥተው ቅዱስ በአሚንን ከወደቀበት አነሱት::
+በወቅቱም ንጉሡ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ "አጽመ ሰማዕታትን ሰብስቡ: በመከራው አልፈው በእድሜ ካሉትም መካከል መምጣት የሚችሉትን አምጡልኝ" ብሏልና ቅዱስ በአሚንን የመሰሉ 72 ክቡራን ተገኙ:: ከእነርሱም መካከል ታላቁ አባ ኖብና አባ ዘካርያስ ይገኙበታል::
+እነዚህ አበው ቅዱሱን ንጉሥ ባርከውት ሲመለሱ ቅዱስ በአሚን ወደ እስሙናይን ተጉዞ በበዓቱ ተቀመጠ:: በዚያም ደቀ መዛሙርት በዝተውለት እንደ ገና ገዳማዊ ሕይወቱን ቀጠለ:: በበዚያም ሳለ ብዙ ተአምራትን ሠራ::
+ድውያንን ፈወሰ:: መናፍቃንንም በጸሎቱ ከአካባቢው አራቀ:: አንድ ቀንም የሮም ንጉሠ ነገሥት ሚስት ወደ እርሱ ዘንድ መምጣቷን ሰማ:: ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ገብተው "አባ! ንግሥቲቱ ትፈልግሃለች" አሉት::
+እርሱ ግን "እኔ ከምድራዊ ንግሥት ዘንድ ምን አለኝ! አልወጣም" አላቸው:: ደቀ መዛሙርቱ ግን መልሰው "አባ! እዘንላት: በመከራ ውስጥ ናት" ሲሉት "እሺ" ብሎ ወጣ::
+ንግሥቲቱ ምንም ብዙ ሠራዊት ብታስከትል አንጀቷ ታጥፎ ተጐንብሳ ነበር የምትሔደው:: እርሱም በጀሮዋ ጠጋ ብሎ የሕመሟን ምሥጢር ሲነግራት ተገርማ እግሩ ሥር ወድቃ ተማጸነችው:: ነገሩ እንዲህ ነው:-
+ከ15 ዓመታት በፊት አንድ የተባረከ ዲያቆን በቤተ መንግስቷ አካባቢ ይኖር ነበር:: እርሱም (ዮሐንስ ይባላል) የዮሐንስን ራዕይ ቁሞ ዘወትር ያነብላታል:: በዚህ የቀኑ የንጉሡ ባለሟሎች በሃሰት "ሚስትህን ዲያቆኑ እያማገጠ ነው" ሲሉ ለንጉሡ ነገሩት::
+ንጉሡም ነገሩ እውነት ስለ መሰለው ወታደሮቹን ዮሐንስን ከነ ሕይወቱ ባሕር እንዲያሰጥሙት አዘዘ:: ይሕንን የሰማችው ንግስት ለቀናት ስታለቅስ አንጀቷ በመቃጠሉ ታመመች:: እየቆየም ሆዷ ታጠፈ:: ለ15 ዓመትም የሚያድናት አጥታ ተንከራተተች::
+በሁዋላ ግን ሰዎች ስለ ቅዱስ በአሚን ቅድስና ሲናገሩ ሰምታ መጣች:: ለዛ ነው ቅዱስ በአሚን ምሥጢሯን ሹክ ያላት:: ቀጥሎም 2 በጐ ነገርን ፈጸላት:: መጀመሪያ ጸሎት አድርጐ ሆዷን ቢዳስሳት በቅጽበት ድና ቀና አለች::
+2ኛው ግን "ያ የምትወጂው የተባረከ ዲያቆን ዮሐንስ አልሞተም:: መላዕእክት ከባሕር አውጥተው እገሌ በሚባል ደሴት አኑረውታል" አላት::እርሷም ተመልሳ በደስታ ለባሏ ነገረችው::
+ንጉሡም ተጸጽቶ ዮሐንስን ካለበት አስመጣው:: አበውም የሮሜ ሊቀ ዻዻሳት አድርገውት ብዙ መጻሕፍትን ተርጉሟል:: ቅዱስ በአሚን ግን በቅድስና ኑሮ በዚህች ቀን ዐርፎ በዝማሬ ተቀብሯል::
=>አምላከ ቅዱስ በአሚን በጸሎቱ ይማረን:: ከትእግስቱ ይክፈለን:: ከበረከቱም ያሳትፈን::
=>ታሕሳስ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=1.ቅዱስ አባ በአሚን (ጻድቅና ሰማዕት)2.ቅድስት አርምያ3.ቅዱስ ዘካርያስ
=>ወርሐዊ በዓላት1.ቅዱሳን 318ቱ ሊቃውንት2.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ኁሉ አባት)3.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ
=>+"+ አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ክፉውን አሸንፋቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ልጆች ሆይ! አብን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: አባቶች ሆይ! ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃቹሃልና እጽፍላቹሃለሁ:: ጐበዞች ሆይ! ብርቱ ስለ ሆናችሁ: የእግዚአብሔርም ቃል በእናንተ ስለሚኖር: ክፉውንም ስላሸነፋችሁ እጽፍላቹሃለሁ:: +"+ (1ዮሐ. 2:13)
   <<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

Home: ስንክሳር በየዕለቱ የሚነበብ
bottom of page